ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚመደብ የሚገልጽ የሕግ ረቂቅ ለውይይት ቀረበ



  • • ‹‹የፓትርያርኩን ሥልጣን ይገድባል›› በሚል ተተችቷል
  • ‹‹አመራራቸውን በብቃት እንዲያከናውኑ የሚያግዝ ነው›› /የሕግ ረቂቁ/
  • ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚያስተላልፉት በብሔራዊ ቋንቋ ብቻ ይኾናል:: 

  • ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገትና ነባራዊ ኹኔታዎች ጋራ በማገናዘብ ያሻሽላል የተባለው የሕግ ረቂቁ ለውይይት የቀረበው፣ ባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመካሔድ ላይ በሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶሱ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጎች ኹሉ የበላይ ነው የተባለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻያ ረቂቁ÷ ርእሰ አበውና ለካህናቷና ለምእመናንዋ ኹሉ መንፈሳዊ አባት ለኾኑት ለፓትርያርኩ እንደራሴ እንደሚሾም በአንቀጽ 24 ላይ ማስፈሩ ተመልክቷል፡፡ እንደራሴው ‹‹ቅዱስ ፓትርያርኩ ከቤተ ክርስቲያን የተጣለበትን ሓላፊነትና መንፈሳዊ አመራር በሚጠበቀው ብቃትና ደረጃ ለማከናወን እንዲችል የሚያግዝ›› መኾኑ በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ተገልጧል፡ ፡

  •        የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ፓትርያርኩን የሚያግዝ እንደራሴ እንደሚመደብ በሚገልጽና የፓትርያርኩን ሓላፊነትና ተጠያቂነት በጉልሕ የሚያሳዩ አንቀጾችን ባካተተ የሕግ ረቂቅ ላይ እየተወያየ እንደኾነ ተገለጸ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በ1991 ዓ.ም. ያወጣችውን ሕግ ከሌሎች ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ጋር በማጣጣም፣
  • እንደራሴው የሚመደበው የቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ብቻ በሚሳተፉበት ምርጫ ሲኾን፣ ለምርጫው ሦስት ዕጩዎች በፓትርያርኩና በቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ጥቆማ እንደሚለዩ ተጠቅሷል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖት፣ ቀኖናና ትውፊት የማስጠበቅ እንዲሁም ያለአድልዎ የማስተዳደር ሓላፊነት ላለበት ለፓትርያርኩ በእንደራሴነት የሚመረጠው ሊቀ ጳጳስ ማሟላት የሚገባው መመዘኛ በሕጉ መመልከቱ የተጠቆመ ሲኾን መመዘኛው ለእንደራሴው ከ50 - 60 ዓመት የዕድሜ ገደብ ሲያስቀመጥ፣ የአስተዳደር ችሎታና የመንፈሳዊ አመራር ልምድን፣ መንፈሳዊና ዘመናዊ ዕውቀት አጣምሮ መያዝን እንደሚጠይቅም ታውቋል፡፡ ‹‹ግለሰባዊ የሥልጣን ፈላጊነት ስሜት የሚገንበት፣ የፓትርያርኩን ሥልጣን የሚጋፋና መካሠስን የሚያበረታታ ነው›› በሚል አንቀጹን የተቃወሙ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ ምደባው አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘም እንደራሴው በፓትርያርኩ ጥቆማ ብቻ መመረጥ እንዳለበት የቃሉ ትርጉም እንደሚያስገደድ በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡
    የአህጉረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች በአንጻሩ፣ የእንደራሴው ምደባ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ብልሹ አሠራር እንዲታረም የአደረጃጀትና የአሠራርለውጥ ጥናት በማድረግ ላይ ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አመራር መጠናከር የራሱ አስተዋፅኦ አለው በሚል እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡ እንደራሴው ፓትርያርኩን ከማገዝ ውጭ ‹‹ለቅዱስ ፓትርያርኩ ከተሰጡት ተግባራት ውስጥ የሚጋራው የተለየ ሓላፊነት አይኖረውም፤›› በሚል በረቂቁ የሰፈረውን አንቀጽ በመጥቀስ ምደባው ፓትርያርኩን የመጋፋት ሚና እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡ ተጠያቂነትን በተመለከተም ፓትርያርኩን ብቻ ሳይኾን ኹሉንም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ለቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪ ከማድረግ፣ በአስተዳደር በደልና በአመራር ጉድለት የካህናቱንና የምእመናኑን አመኔታና ተቀባይነት ማጣትን ጨምሮ ከሀብትና ንብረት ባለቤትነት ጋራ የተያያዙ ዝርዝር የተጠያቂነት አንቀጾች በረቂቁ በመካተታቸው በፓትርያርኩ አልያም በወቅታዊ እይታ ላይ ብቻ የታጠረ ረቂቅ እንዳልኾነ ያስረዳሉ፡፡
    ጉዳዩ በዋናነት የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ አመራር ከማጠናከር አንጻር ሊታይ ይገባል የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች፣ ምልዓተ ጉባኤው የሕግ ማሻሻያ ረቂቁን በጥልቀት በማዳበር የቅዱስ ሲኖዶሱ ሉዓላዊ ሥልጣን በማንም የማይገሠስበት መሣርያ አድርጎ እንደሚያጸድቀው እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ በዓላት ላይ እንዳስፈላጊነቱ እየተገኘ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሚሰጠው እንዲሁም በብዙኃን መገናኛ መንፈሳዊ መልእክት የሚያስተላልፈው በአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ እንደሚኾን በሕግ ማሻሻያ ረቂቁ ላይ መስፈሩ ተጠቅሷል፡፡
  • Source: Addis Admass

    No comments:

    | Copyright © 2013 Lomiy Blog