‹‹ኦሮሞነት አደጋ ውስጥ ገባ የሚለው ሚዛን የማያነሳ መፈክር ነው››


አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ :: 
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን በመቃወም በተለያዩ የኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲዎች የተነሳው ተቃውሞ ለኦሮሞነት ያላዘነ ባዶ መፈክር ነው ሲሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጥናት አማካሪና የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኩማ ደመቅሳ ገለጹ፡፡ 
አቶ ኩማ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፣ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተፈጠረው ተቃውሞና ውጥረት ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች እንዳሉት፣ እነሱም ኦሮሚያን ቆርጦ ለማስቀረት የታለመ ማስተር ፕላን ነው የሚልና ፕላኑ ለምን በሚስጥር ተሠራ የሚል ሥጋት የፈጠሩት ናቸው ብለዋል፡፡ 
የተዘጋጀው ማስተር ፕላን ምንም ዓይነት የድንበር እንዲሁም የአስተዳደር ጥያቄ አለመያዙን የተናገሩት አቶ ኩማ፣ ሌላ የፖለቲካ ተልዕኮ ያላቸው ግን ጉዳዩን ከኦሮሞነት ጋር በማያያዝ የኦሮሞ ሕዝብን እያደናገሩ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ‹‹ኦሮሞነት አደጋ ውስጥ ገባ የሚለው ባዶ መፈክርና ሚዛን የማያነሳ ክርክር ነው፤›› ያሉት አቶ ኩማ፣ ይህንን በማለት ለማደናገር የሚፈልጉ አጀንዳ ያላቸው ክፍሎችን ማብራሪያ በመስጠት መመለስ አይቻልም ብለዋል፡፡

‹‹ጉዳዩ የሕዝብ አይደለም፡፡ ከሕዝብ አንፃር ችግር አለ ብለን አናስብም፤›› ሲሉ ችግሩ የመደናገርና የሌሎች አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንደሆነና እልባትም እንደሚያገኝ ጠቁመዋል፡፡ 
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባለፈው ዓርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዓርብ ዕለት መቀዛቀዙን ገልጿል፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋርም ውይይት እየተደረገ ችግሩ ከመባባስ ይልቅ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ብሏል፡፡
ከሳምንት በፊት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በመጠኑ የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ ባለፈው ረቡዕ በከፍተኛ ደረጃ ተቀጣጥሎ ከዩኒቨርሲቲ ቅጥር ማለፉ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ በባሌ ዞን በመደወላቡና በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ተቃውሞው ተስፋፍቶ ነበር፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው ተቃውሞ ባለፈው ሐሙስና ዓርብ በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ላይ ውጥረት ፈጥሮም ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ በግምት ወደ 150 የሚሆኑ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ‹‹የኦሮሞ ጥያቄ ይከበር፣ ፍትሕ ለኦሮሞ፣ የአዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ መስፋፋት እንቃወማለን…›› የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ተስተውለዋል፡፡
ይህ የሆነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተማሪዎቹን ባለፈው ሐሙስ ጠዋት ሰብስበው ካነጋገሩና በማግሥቱ በጉዳዩ ላይ እንደሚወያዩ ከገለጹላቸው በኋላ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ከግቢው ውስጥ አልፎ አልወጣም፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ውጪ በርካታ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ተስተውለዋል፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ለአብነትም በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) እና በቡራዩ ከተሞች ተመሳሳይ ተቃውሞ ተከስቶ እንደነበር የአካባቢው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከቅጥር ግቢያቸው በመውጣት መጠነኛ ተቃውሞ ባለፈው ዓርብ ያካሄዱ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፖሊስ መበተናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በቡራዩ ከተማ ተመሳሳይ ተቃውሞ ታይቶ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በተካሄደው ተቃውሞ በተለይ በአምቦ፣ በመደወላቡና በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተው ተቃውሞ ከባድና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭትን ያስከተለ መሆኑን፣ በዚህም በርካታ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የዓይን እማኞች በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እየገለጹ ነበሩ፡፡
ይሁን እንጂ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሐሙስ ባወጣው መግለጫ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 11 መሆኑንና 70 ያህል ተማሪዎች ደግሞ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በተጣለ ፈንጂ መቁሰላቸውን ገልጿል፡፡
‹‹በኃይል በታጀበ ግርግር ሳቢያ በመደወላቡ የሦስት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡ በተለይም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተቀሰቀሰው ሁከት ወደ ከተማ በመዝለቁ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት በአምቦ ከተማ ቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ ላይ በተደረገው የዘረፋ ሙከራና ሌሎችም ሕገወጥ የነውጥ እንቅስቃሴዎች፣ በአምቦና ቶኬ ኩታዩ ከተሞች የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡ በፌዴራልና በክልል የፀጥታ ኃይሎች ትብብር ሁከቱ በተፈጠረባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት ተችሏል፤›› ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መግለጫ ያትታል፡፡
ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች በቴሌቪዥን የእግር ኳስ ጨዋታ በመከታተል ላይ በነበሩ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ፈንጂ በመወርወር 70 ያህል ተማሪዎችን ያቆሰሉ መሆኑና የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
‹‹በተደረገው ማጣራት ከበስተጀርባ በመሆን ሁከቱን በማነሳሳትና በማቀነባበር ተግባር ላይ የተሰማሩ ጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፤›› ሲል መግለጫው ያስረዳል፡፡
ተቃውሞው የተቀሰቀሰው በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኘውን የኦሮሚያ ልዩ ዞን በልማት ለማስተሳሰር የተነደፈውን የተቀናጀ የልማት ማስተር ፕላን አስመልክቶ፣ ከፕላኑ ፋይዳና ዓላማ ጋር የሚቃረን መሠረተ ቢስ አሉባልታ በአንዳንድ ወገኖች በስፋት በመሰራጨቱ መሆኑን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በመግለጫው አስታውቋል፡፡
 Source: Reporter

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog