ዓለም
ሁሉ ጠላን፤ በየትም አገር እየሄድን ‹‹የሙጢኝ!›› ከራሳችን መሬት በጉልበት እየተነቀልን፣ ከራሳችን ቤት
እየተባረርን፤ ከተወለድንበትና ከአደግንበት አካባቢ እየተፈናቀልን፣ ጭራውን ቆልምሞ እንደሚሮጥ ባለቤቱ እንዳባረረው
ውሻ በአገኘነው አቅጣጫ እየሮጥን፣ እጃችንን እያርገበገብን
‹‹የሙጢኝ!›› እንላላን፤ የፈራነውን ሞት በየመንገዱ እናገኘዋለን፤ ሞትን ሸሽተን ሞትን ያጋጥመናል፤ የሞቱ ልዩነት
አይታየንም፤ በየመንገዱ የሚያጋጥመው ሞት የውርደት ሞት ነው፤ የብቸኛነት ሞት ነው፤ ዘመድ-ወዳጅ ለቀብር
የማይገኝበት ሞት ነው፤ ሠለስት፣ አርባ፣ ሙታመት የማይወጣበት ሞት ነው፤ ባዕድ ምስጥ ያላሳደገውን አካል የሚበላበት
ነው፤ የሞት ሞት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ከአገር አስወጥቶ ባዶ መሬት ብቻ ይፈልግ ይመስል የወያኔ ሎሌዎች በማስፈራራት ሁሉም አገሩን እየተወላቸው እንዲሄድ ያቀዱ ይመስላል፤ ጥንት ኢሰመጉ በምሠራበት ጊዜ በየጊዜው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሰዎችን በማስፈራራት ሰላማቸውን ለመረበሽ ወደስደት ወይም ወደወንጀል ተግባር የሚመሩ የወያኔ አባለች ነበሩ፤ አሁን እንደገና ብቅ ማለት ጀምረዋል፤ ሕጋዊ ሥርዓት እየላላ ጉልበተኞች በግላቸው ለዘረፋና ለቅሚያ እየተሰማሩ ይመስላል፡፡
ስለራሴ ላውራ፤ ከእኔ የሚፈልጉት ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፤ የሚፈልጉት የምኖርበትን አፓርትመንት እንደሆነም አላውቅም፤ በእኔ ቤት ያለ ሀብት የሚባል ለወያኔ አገልጋዮች የሚጠቅም ሁለት የገብረ ክርስቶስ ስዕሎች ብቻ ናቸው፤ (በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ስዕሎች ለመግዛት የሚፈልግ ያነጋግረኝ)፤ ከዚህ ሌላ ለወያኔ ዋጋ የሌላቸው መጻሕፍት ናቸው፤ ስለዚህም አሁን በእኔ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት እኔን ወደስደት ለመግፋት የሚደረግ ሙከራ ይሆናል፤ በ1992 ግድም ተሞክሮ ነበር፤ አልሠራም፤ ዛሬ ይበልጥ አይሠራም፤ ለማናቸውም ምክንያቱን በትክክል ለማወቅ ባልችልም በእኔ ላይ ዘመቻ መጀመሩን አንድ በቅርብ ከማውቀው ወያኔ በትክክል ተረድቻለሁ፤ ይህንን ዘመቻ በመምራት ላይ ያለውንም ሰው ማንነት ተነግሮኛል፡፡
ይህ አገር የአንድ ጉልበተኛ ቡድን ነው ብዬ አልቀበልም፤ የአባቶቼና የእናቶቼ፣ የኤቶቼና የቅድማያቶቼ አጥንትና ደም የገነባው አገር ነው፤ ማንም ለስደት አይዳርገኝም፤ ማንም አስፈራርቶ ኢትዮጵያዊነት መብቴን መግፈፍ አይችልም፤ አልፈቅድለትም፤ በግልጽ በማያጠራጥር ቋንቋ ኑሮዬም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም እዚሁ ነው፤ ከኢትዮጵያ አፈር የሚለየኝ የለም፡፡
እኔን ለማጥቃት ላሰፈሰፉት ወያኔዎችና ሎሌዎቻቸው አንድ እውነት ልንገራቸው፤– በፈለጉትና በተመቻቸው መንገድ በእኔ ላይ በጉልበታቸው ግፍ ቢፈጽሙ ነገ በነሱ ላይ የባሰ ግፍ እንደሚደርስባቸው ይወቁት፤ ሁልጊዜም ከሕግ የወጣ ጉልበተኛነት ጉልበተኛነትን ያነግሣል፤ በመግደል ድል ይገኛል ብለው የሚያምኑ ወያኔዎች ትንሽ ቆም ብለው ያስቡ፤ በመሞትም ድል ይገኛል፤ በመሞትም ማሸነፍ ይቻላል፡፡
በእኔ ላይ የዘመተው ወያኔ ወይም ሎሌ ማናቸውም ሥራ ውጤት እንዳለው ማወቅ አለበት፤ አንድ ነገር አድርጎ ምንም ዓይነት ውጤት አያስከትልም ብሎ ማሰብ ድንቁርና ነው፤ ይህ የሳይንስ ሕግ ነው፤ For every action there is a reaction ይላል!
አሰግድ ታመነ
No comments: