በደ/ጎንደር ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አደራጆች፣ መጋቢት 20/2007 ዓ.ም በደብረታቦር ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ዜጎች ድብደባ እንደደረሰባቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አደራጆችን ጨምሮ በሰልፉ ከተገኙት መካከል 20 ያህል ዜጎች በገዥው ፓርቲ የደህንነት ኃይሎች ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን በደ/ጎንደር ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ፀኃፊ አቶ ሰለሞን ታደሰ በትናንትናው ዕለት በደህንነቶች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰበት ገልጾልናል፡፡
ትናንት መጋቢት 24 ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ ‹‹ትፈለጋለህ›› ተብሎ በደህንነቶች ከተያዘ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመበት የገለጸው አቶ ሰለሞን ታደሰ በከተማው ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንዲያድር ከተደረገ በኋላ ዛሬ ጠዋት መፈታቱን ገልጾአል፡፡ በተመሳሳይ በሰልፉ ላይ የተገኙት ዜጎችና የሰማያዊ ፓርቲ አደራጆች ‹‹ሁከትና ብጥብጥ ልትፈጥሩ ሞክራችኋል›› በሚል እስርና ድብደባ ተፈጽሞብናል ብለዋል፡፡
ማታ ላይ ያለምንም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተያዘ በኋላ ደብደባ ተፈፅሞበት ታስሮ ያደረው አቶ ሰለሞን ጠዋት 2፡30 ላይ የከተማው የፖሊስ አዛዥ መቶ አለቃ ፈንቴ እና የፀጥታ ሰራተኛው ትዕዛዝ ‹‹ልቀቁት›› ተብሎ እንደተፈታ ገልጾአል፡፡
No comments: