አፍሪካና የማያባራው እልቂት

የውጭ ሀገር ዜጎች ጥላቻ ዳግም በደቡብ አፍሪቃ መቀስቀሱ፣ በፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝ በምትመራው አነስተኛዋ የአፍሪቃ ሀገር የምርጫ ሂደት፣ እንዲሁም ሶማሊያን የሚመለከት ጉባኤ በብራስልስ የተሰኙት ርዕሰ ጉዳዮች በትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን ከተካተቱት ጥንቅሮች ዋነኖቹ ናቸው።
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ፖርት ኤሊዛቤዝ በተሰኘው አካባቢ የውጭ ሀገር ጥላቻ የተጠናወታቸው ግለሰቦች ሰሞኑን የሶማሊያውያን የሆኑ ንብረቶችን ሲመዘብሩ፣ ሲዘርፉ ብሎም እሳት ሲለቁባቸው ቆይተዋል። ከ1200 የሚበልጡ ሶማሊያውያንም ለህይወታቸው በመስጋት ቤት ንብረታቸውን ጣጥለው በሽሽት ላይ ይገኛሉ። አብዛኞቹም ታሪክ እራሱን እንዳይደግም አጥብቀው ሰግተዋል። የዛሬ አምስት ዓመታት ግድም
እጅግ የተቆጡ ስብስቦች በመላ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ጥቁር አፍሪቃውያን ላይ ድንገት ተነስተው ጥፋት ማድረሳቸው ይታወሳል። በያኔው ቁጣ በቀሰቀሰው ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ቤቶች ዶግ አመድ ሆነዋል፣ ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። የዶቼ ቬሌው ሰብሪ ገቬንደር ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በፍርሀት ተውጠው የሚገኙ ስደተኞችን አነጋግሮ የሚከተለውን ልኮልናል፤ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

የ30 ዓመቱ ፍሬዲ ምባዬ በዜግነት ብሩንዲያዊ ነው። ወደ ደቡብማ አፍሪቃ የመጣው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው። ላለፉት ሶስት ዓመታት የዕለት ጉርሱን የሚያሰባስበው የወደብ ከተማ በሆነችው ደርባን ውስጥ ከተሰማራበት የመኪና ጥበቃ ስራ ከሚያገኘው ገቢ ነው። የሚኖረው ከታናሽ ወንድሙ ጋር በአንድ መጠለያ ውስጥ ነው። ህይወት ሁለቱንም ዕለት በዕለት ታታግላቸዋለች። ጎናቸውን ለሚያሳርፉበት መጠለያ እና ለምግባቸው የሚሆን በቂ ገንዘብ ለማግኘት ሠርክ ተጨማሪ ስራ ፈልገው መታተር አለባቸው። ያም ብቻ አይደለም እንዲያ ላይ እታች ብለው ከሚያገኟት ገቢ ላይም ቆጥበው ሀገር ቤት ለሚገኙት ሰባቱ እህቶቻቸው እና ሁለቱ ወንድሞቻቸው መላክ ይጠበቅባቸዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ፍሬዲን እጅግ የሚያጨንቀው ያ አይደለም። ለፍሬዲ ጭንቀቱ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ አፍሪቃውያን ስደተኞች ላይ ዳግም የተቀሰቀሰው ጥላቻና ጥቃት ነው።
«በነገሩበጣምልባችንተነክቷል።እነዛንሰዎችምንእንደነካቸውእንጃ።ምንአለባይሰርቁን፣ምንአለባይመዘብሩን።»

ደቡብ አፍሪቃ የውጭ ዜጎች ጥላቻና ጥቃት

ዴቪድ ፒቶሾም ቢሆን ተመሳሳይ ስሜት ነው ያለው። ከኮንጎ ተነስቶ ደቡብ አፍሪቃ የገባው ከአስር ዓመታት በፊት ነው። የሚተዳደረውም ከጥበቃ በሚያገኘው ገንዘብ ነው። የዛሬ አምስት ዓመታት ግድም በደቡብ አፍሪቃ ተቀስቅሶ ከነበረው የውጭ ሀገር ነዋሪዎች ጥላቻ ቀዳሚውንና ዋነኛውን ያስታውሳል። በቁጣ የተሞሉ ሰዎች በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የሚገኙ አፍሪቃውያን ስደተኞችን ሲያጠቁም ከሚኖርበት ስፍራ ሆኖ ታዝቧል። ንብረትነታቸው የሶማሌያውያን የሆኑ መደብሮች በእሳት ተንቀልቅለዋል። በስተመጨረሻም ጥቃት ፈፃሚዎቹ የ62 ሰዎችን ልሳን እስከወዲያኛው ዘግተዋል፤ 47.000 ሰዎች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ጣብያዎች እንዲጎርፉም ተገደዋል። ዳግም ያ ቁጣ አገርሽቶ በርካታ ቤቶችን የእሳት ነበልባል ሲያንቀለቅላቸው ዴቪድ ፍርሀት ገብቶት እጅግ ርዷል።
«ለእኔ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ መቆየት አያስደስተኝም፤ ወይንም ጥሩ ስሜት አይሰጠኝም። እዚህ ተቀምጦ ያን ሁሉ ነገር መመልከትም አልፈልግም። ከእዚህ ሀገር መውጣት ነው የምሻው፤ ምክንያቱም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚሆነው ነገር ሁሉ አንድ ቀን እኔንም መጉዳቱ አይቀርም።»
የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ማናቸውም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች ፈፅሞ ተቀባይነት የላቸውም ባይ ነው። ፖሊስ ከ200 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሎዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ፖሊስ ጥቃቱ የተፈፀመው ከውጭ ሀገር የመጡ ስደተኞችን በሚጠሉ ግለሰቦች አይደለም ሲል አስተባብሏል። ይልቁንስ ጥቃቱ የተፈፀመው በወንጀለኞች ነው ሲል ተደምጧል። የሠብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የሐይማኖት ተቋማት መንግሥት አፍሪቃውያን ስደተኞች በአግባቡ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተገቢውን ስራ አላከናወነም ሲሉ ይተቻሉ። እናም መንግሥት ጥቃት በተፈፀመ ቁጥር ብጥብጡን የሚያወግዝ የመግለጫ ጋጋታ ከሚያቀርብ ይልቅ የበለጠ ሊሰራ ይገባል ይላሉ። ዶክ ፊስመር የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ናቸው።
«እነዚህ ሁሉ ነገሮች በእዚህ መልኩ ከቀጠሉ ለሀገራችን መፃዒ ዕጣ መልካም አይደሉም። ምክንያቱም እንደእነዛ አይነት በርካታ ሰዎች አሉንና። መንግሥት ይህን ጉዳይ እጅግ በጥንቃቄ ሊመለከተውና ምን ሊያደርግ እንደሚገባው ከውሳኔ ላይ መድረስ አለበት፤ ምክንያቱም ነገሩ እየተደጋገመ ነውና። ስለእዚህ የሆነ ነገር ማድረግ አለብን።»
ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳያችን ስንሻገርም ከእዛው ከደቡብ አፍሪቃ ብዙም አልራቅንም። አፍሪቃ ውስጥ ፍፁም ዘውዳዊ በሆነ ስርዓት ወደምትተዳደረው አነስተኛዋ የደቡብ አፍሪቃ ሀገር ስዋዚላንድ ነው የምናቀናው።
በእዚህች አነስተኛ ሀገር መስከረም 10 ቀን 2005 ዓም የምክር ቤት አባላት ምርጫ ተካሂዷል። ሆኖም ፖለቲካዊ ለውጥ የመምጣቱ ነገር ግን እምብዛም ተስፋ የሚጣልበት አይነት አይደለም። ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ በደቡብ አፍሪቃ እና ሞዛምቢክ መሀከል የምትገኘውን ትንሽዬ ሀገር ሲመሩ 27 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ንጉሡ ከስልጣናቸውም ሆነ ከአገዛዝ ስርዓታቸው አንዳች እንዲቀየር የሚፈልጉ አይነት አይደሉም። ሀገሪቱ ግን ዲሚክራሲያዊ ሂደት በአስቸኳይ የሚያሻት ናት። የማኅበረሰቡ ሰቆቃ፣ የምጣኔ ሀብቱ ድቀት ብሎም የንጉሣውያኑ ቅጥ አልባ ብክነት መረን ለቋል። እንዲያም ሆኖ ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ አሁንም ሰጥ ለጥ አድርገው መግዛት ነው የሚሹት። ዓለም ግን ያሸበረቁ ስዕላቸውን እንዲያይላቸው ይፈልጋሉ። ምርጫ በስዋዚላንድ፤ ጁሊያ ሐን የላከችውን ዘገባ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን።
የሚጨፍሩት፣ የሚዘምሩት ለንጉሡ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፤ ዳሌያቸው ላይ ጣል ካደረጉት ብጣቂ ጨርቅ ውጪ ከፊል ርቃናቸውን፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ዓርማ በሚወክለው ሠማያዊ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀላማት አጊጠው ለንጉሡ ይጨፍራሉ።
ከምርጫው ቀደም ብሎ በሣምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነ በእዚህ መሰሉ ስነስርዓት ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ የሚሽቶቻቸውን ቁጥር ለማብዛት ከውሳኔ ላይ ደርሰዋል። እናም ትምህርቷን ከአጠናቀቀች ገና ብዙም ያልቆየችው የ18 ዓመቷ ወጣት 15ኛዋ ውሃ አጣጪያቸው ትሆናለች። የምዋሲቲ ምኞት ተሟልቷል። የ45 ዓመቱ ጎልማሳ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ስዋዚላንዶችን ሰጥ ለጥ አድርገው ነው የሚያስተዳድሩት።
ትናንት ስዋዚላንዶች የምክር ቤት አባላትን እንዲመርጡ ተፈቅዶላቸዋል። በእርግጥ ግን ምርጫው አንዳች የሚቀይረው ነገር አይኖርም ሲሉ በስዋዚላንድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሰረት የሚሰራው «የስዋዚላንድ ወጣቶች ምክር ቤት» ዋና ፀሀፊ ማክስዌል ድላሚኒ ይተቻሉ።
«ፍፁም ዘውዳዊ በሆነ አገዛዝ ስር ነው የምንገኘው፤ ምክንያቱም ንጉሡ ፈላጭ ቆራጭ ናቸው። ሕዝቡን የተጠቀሙበት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በስዋዚላንድ ተዓማኒ ምርጫ ተካሂዷል ብሎ እንዲያምን ለማታለል ነው።»
በምዕራባዊያን መለከያ ሲታይ ምርጫ ተብየው አንዳች ዲሞክራሲያዊ ይዘት የለውም። የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል። «ፑዴሞ» ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ በኅቡዕ እና ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በስደት ነው የሚንቀሳቀሰው። የምክር ቤት ተወካዮቹ ነፃ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ተደርገው ነው የሚታዩት ግን ከጎሣ መሪዎች ድጋፍ ሊኖራቸው ይገባል። ከ65ቱ የምክር ቤት አባላት መካከል አስሩ በቀጥታ የሚሰየሙት በንጉሡ በራሳቸው ቀጥተኛ ቀጭን ትዕዛዝ ነው። የተቀሩትም ቢሆኑ የንጉሡ ይሁንታ ያስፈልጋቸዋል። ከእዚያ ባሻገር ንጉሡ ከህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላቱ ሁለት ሶስተኛውን፣ ጠቅላይ ሚንስትሩን፣ ካቢኔውን ብሎም ከፍተኛ ዳኞችን እራሳቸው በቀጥታ ይሾማሉ። ምክር ቤቱ ሙሉ በሙሉ ጥርስ አልባ ነው። ሕግ አውጪውም፣ ሕግ አስተርጓሚውም፣ ሕግ አስፈፃሚውም እኚሁ አንድ ንጉሥ ናቸው። ሠማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ እንዲሉ በስዋዚላንድ ትንፍሽ ማለት አይፈቀድም። የመብት ተሟጋቹ ማክስዌል ድላሚኒ ከጭቆናው ገፈት ቀማሾች አንዱ ነው።
«ንጉሡ በሕዝቡ የሚደረግባቸውን ሂስ በቀና የሚቀበሉ አይነት አይደሉም። ስለእዚህም በየጊዜው ሰዎች በዘፈቀደ ወህኒ ይወረወራሉ፣ አካልን የሚያሰቃይ ተግባር ይፈፀምባቸዋል አለያም ከሀገር እንዲሰደዱ ይገደዳሉ። እኔ እራሴ መንግሥት በሀሰት በመሰረተብኝ ሁለት ክሶች ምክንያት ከተጣልኩበት ዘብጥያ የወጣሁት በዋስ ነው።»
ድላሚኒ እምቢኝ ሲል በተደጋጋሚ ንጉሡ ላይ ተቃውሞ አሰምቷል። ከዛሬ ሁለት ዓመታት በፊት ንጉሡን በመቃወም በመቶዎች የሚቆጠሩ ስዋዚላንዶች ወደ አደባባይ ሲወጡ ድላሚኒም ተቀላቅሏቸው ነበር። በእርግጥ ሕዝቡ በነቂስ «ሆ!» ብሎ የወጣበት ሰልፍ አይደለም። ያኔ በሰሜን አፍሪቃ ሃገራት የተቀሰቀሰው ዓመፅ ያነሳሳቸው ስዋዚላንዶች በሀገሪቱ ላይ የተጫነው የድህነት መርግ እንዳንገፈገፋቸው ለመግለፅ ነበር የተሰለፉት።
ስዋዚላንድ በዓለማችን ከሚገኙት 10 እጅግ ድሀ ሃገራት መካከል ትመደባለች። ከሶስት እጁ ሁለት ያህሉ የሚኖረው እጅግ ከድህነት በታች በሆነ ሁናቴ ውስጥ ነው። የሀገሪቱ የገንዘብ ምንጭ የውጭ ሃገራት በተለይም ደቡብ አፍሪቃ ናት። በዋናነት ስኳርን መሰረት ያደረገው የውጭ ንግድ የስኳር ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ በመውደቁ የተነሳ በከፍተኛ ተጎድቷል። ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ ግን ዛሬም በ13 ቤተመንግስቶቻቸው ውስጥ ተንፈላሰው የተንደላቀቀ ህይወት ይመራሉ። ሲያሻቸው እመር ብለው የግል ጄታቸውን ሊያስነሱ አለያም ቄንጠኛ ሊሞዚናቸውን ሊያሽከረክሩ የሚገዳቸው የለም። ሀገራቸው ግን በሙስና ነቅዛለች። ከነዋሪዎቹ ከሶስቱ አንዱ ከኤች አይ ቪ ቫይረስ ጋር ነው የሚኖረው። በዓለማችን የተዳቀቀች ባሕር አልባዋ ትንሽዬ ሀገር ስዋዚላንድ ትናንት በንጉሡ ጫና ስርም ቢሆን የምክር ቤት አባላት ምርጫ አከናውናለች።
አሁን ደግሞ ሶማሊያንና መካከለኛው አፍሪቃን በአጭሩ እንዳስሳለን። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሶማሊያን መልሶ ለመግንባት በሚል 1.8 ቢሊዮን ዩሮ ርዳታ ለመለገስ ቃል መግባቱ በእዚሁ ሣምንት ከወደ ብራስልስ ተሰምቷል። በዕርዳታ መልክ የሚቀርበው ገንዘብ በዋናነት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብትና የፀጥታ ሁናቴ ለማጠናከር ያግዛል ተብሏል። የሶማሌ መሪዎች እና ከ50 ሃገራት የተውጣጡ ልዑካናት ሶማሊያን ለመደገፍ ብራስልስ ውስጥ በተካሄደው ጉባኤ ተገናኝተው ተነጋግረዋል። በሶማሊያ የፍትሕ ስርዓት እንዲገነባ፣ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲዳብርና የዕለት ተዕለት የፀጥታ ሁናቴው እንዲሻሻል እገዛ ያደርጋል የተባለለትን ዕቅድም መንደፋቸው ታውቋል።
መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ውስጥ ደግሞ የሴሌካ ጥምረት የተሰኘ አማፂ ቡድን ሀገሪቱን በማመስ እና ሕዝቡን በማስጨነቅ ላይ ይገኛል። ይህ የተለያዩ አማፂያን ኅብረት የፈጠሩበት የሴሌካ አማፂያን ቡድን በሀገሪቱ ስልጣን የተቆናጠጠው መጋቢት 15 ቀን፥ 2005 ዓም ሲሆን፤ የሀገሪቱን ለ10 ዓመታት የመሩትን ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ቦዚዚን በማስወገድ ነበር ወደ መንበሩ የወጣው። የሴሌካ ጥምር የዓማፂያን ቡድን ስርዓት አልባ በሆነው የሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ሲንቀሳቀስ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል። ቡድኑ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ ሚካኤል ጆቶዲያን የሀገሪቱ ርዕሠ ብሔር አድርጎ ሲሾም አማፂያኑ ሀገሪቱን በመዝረፍ፣ በርካቶችን በመግደልና ወደ 180,000 የሚሆኑ ነዋሪዎችን በማፈናቀል ይከሰሳሉ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ
Source www.dw.de

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog