በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ለሆነው ከአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ጋር ለሚያገናኘው የአዲስ አበባን ውጫዊ ቀለበት መንገድ ለመገንባት የሚያስፈልገውን 4.3 ቢሊዮን ብር ብድር፣ የቻይናው ኢምፖርት ኤክስፖርት (ኤግዚም) ባንክ ፈቀደ፡፡
በስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘውና በአሁኑ ወቅት ግንባታው 85 በመቶ የተጠናቀቀው በዓይነቱ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የፍጥነት መንገድ፣ በአዲስ አበባና በአዳማ መካከል ያለውን ርቀት ወደ 80 ኪሎ ሜትር የሚያሳጥር ነው፡፡ የዚህ መንገድ ግንባታ በዘንድሮው በጀት ዓመት የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ መግቢያ ላይ ተቀባይና ወደ መሀል ከተማ ሊያስገቡ የሚችሉ ተጨማሪ መንገዶች ካልተገነቡ፣ የፍጥነት መንገዱ እንዲሰጥ የሚፈለገውን ፈጣን ትራንስፖርት እንደሚያስተጓጉለው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተገንዝቦታል፡፡
በመሆኑም የፍጥነት መንገዱ መነሻ ወደሆነው አቃቂ ቃሊቲ የሚያደርስ የአዲስ አበባ ውጫዊ የቀለበት መንገድ መገንባት እንዳለበት መወሰኑን፣ ከባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ውጫዊ የቀለበት መንገዱ በፍጥነት ተጀምሮ መጠናቀቅ እንደሚገባው በማመንም፣ የፍጥነት መንገዱን ግንባታ በማከናወን ላይ ለሚገኘው የቻይናው ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ የቀለበት መንገዱን እንዲገነባ ከወራት በፊት ሰጥቷል፡፡
ይህ ኩባንያ የአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ከሚጠይቀው ስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ ከፍተኛውን ድርሻ በብድር ያቀረበ ሲሆን፣ ውጫዊ የቀለበት መንገዱን እንዲሠራ የተወሰነውም በተመሳሳይ የግንባታውን ወጪ ራሱ በብድር እንዲያቀርብ በተደረሰ ስምምነት ነው፡፡
በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ውጫዊ የቀለበት መንገድ በአጠቃላይ 28.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ አጠቃላይ ወጪውም 4.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡
ኩባንያው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር ባደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ላለፉት ወራት የግንባታውን ወጪ በብድር ለማግኘት ሲያፈላልግ መቆየቱን፣ በተጠናቀቀው ሳምንት ውስጥ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ እንደተፈቀደለት የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
የቀለበት መንገዱ ግንባታ በሁለት የአዲስ አበባ አቅጣጫዎች የሚካሄድ ሲሆን፣ አንደኛው ከየረር በመነሳት ከፍጥነት መንገድ መነሻ አቃቂ ቃሊቲ የሚያገናኝ 14.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚኖረው፣ ሁለተኛው የቀለበት መንገድ አካል 13.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ሆኖ ከለቡ አካባቢ በመነሳት ከፍጥነት መንገዱ የሚያገናኝ መሆኑን መረጃው ያስረዳል፡፡
Souce: http://www.ethiopianreporter.com/
No comments: