የሜርክልን የእጅ ስልክ አሜሪካ ጠለፈች!

የጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል የእጅ ስልክ በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የስለላ ተቋም ተጠልፏል የሚለዉ ዜና እያነጋገረ ነዉ። ዩናይትድ ስቴትስ ድርጊቱን እንዳልፈፀመች በመጥቀስ አስተባብላለች። ጉዳዩ በአውሮጳ መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ጀርመን የመራሂተ መንግስቷ ስልክ ሳይሰለል አይቀርም በሚል በበርሊን የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደርን ዛሬ ለማነጋገር መጥራቷ ተዘገበ። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ በጀርመን ለአሜሪካኑ አምባሳደር ጆን ኤመርሰን በዚህ ረገድ የጀርመንን ግልጽ አቋም እንደሚያቀርቡም ተገልጿል። የጀርመን መገናኛ ብዙሃን የአሜሪካን የስለላ ተቋም NSA የመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን የእጅ ስልክ ሳይጠለፍ አልቀረም የሚል መረጃ ይፋ አድርገዋል። ዋሽንግተን ግን አስተባብላለች። ይህ ከተሰማ በኋላም ሜርክል ራሳቸዉ ለፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ስልክ በመደወል የተባለዉ እዉነት ከሆነ ፍፁም ተቀባይነት የለዉም ማለታቸዉን ቃል አቀባያቸዉ ሽቴፈን ዛይበርት ገልጸዋል። የመከላከያ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዚየር በበኩላቸዉ፤

«የሰማነዉ እዉነት መሆኑ ከተረጋገጠ በጣም መጥፎ ነዉ። አሜሪካዉያን እዉነተኛ ጓደኞቻችንነበሩ አሁንም ናቸዉ፤ ሆኖም እንዲህ ሊቀጥል አይችልም።»
ኋይትሃዉስ ኦባማ ትናንት ከሜርክል ጋ ባደረጉት የስልክ ዉይይት የአሜሪካን የስለላ ተቋም እሳቸዉን እንደማይሰልል ማረጋገጣቸዉን ቢገልጽም ከዚህ ቀደም ስለመደረጉ ያለዉ የለም። የኋይት ሃዉስ ቃል አቀባይ ኤይ ካርኔ፤
«እኔ ልገልጽ የምንችለዉ ፕሬዝደንቱ ዩናይትድ ስቴትስ መራሂተ መንግስቷን በወቅቱ እንደማትሰልል፤ ወደፊትም እንደማትሰልል እንዳረጋገጡላቸዉ ነዉ። ዩናይትድ ስቴትስ ከጀርመን ጋ ሰፊ የጸጥታ ችግሮችን በተመለከተ ላለን የቀረበ ትብብር ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች።»
ስለሜርክል ሞባይል መጠለፍ የተሰማዉ የNSA በቀድሞዉ ባልደረባ ኤድዋርድ ስኖዉደን ጉዳዩን አጋልጦ በርካቶች መራሂተ መንግስቷ ነገሩን ያደባብሳሉ የሚል ጥርጣሬ እየተሰነዘረ ባለበት ወቅት ነዉ። የስልካቸዉ መጠለፍ ያስቆጣቸዉ ሜርክል በሳምንቱ መጀመሪያ ከ70 ሚሊዮን በላይ የስልክና ኢሜል ልዉዉጦች መጠለፋቸዉ ካናደዳት ፈረንሳይ መሪ ፍራንስዋ ኦሎንድ ጋ በጉዳዩ ላይ ዛሬ እንደሚነጋገሩ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ከብራስልስ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ብራስልስ ላይ የተሰባሰቡት የአዉሮፓ ኅብረት አባል መንግስታት መሪዎች የግለሰብ ዜጎችም ሆነ የመሪዎች የግል ጉዳይ ላይ የሚደረግ ስለላ ተቀባይነት እንደማይኖረዉ አመልክተዋል። የፈረንሳይ የዜና ወኪል የኅብረቱ የፍትህ ኮሚሽነር ቪቫነ ሬዲንግ ቃል አቀባይ ኮሚሽነሯ መረጃን የመከላከል ርምጃ የአንጌላ ሜርክል የእጅ ስልክንም ሆነ የግለሰብ ዜጎችን የኢሜል ልዉዉጥ ላይ በእኩልነት ተግባራዊ ልሆን ማለታቸዉን ዘግቧል። ኮሚሽነሯ የኅብረቱ ጉባኤ ማብራሪያ የሚጠይቅበር ሳይሆን ርምጃ የሚወስድበት ጊዜ አሁን ነዉ ማለታቸዉም ተጠቅሷል። ከወራት በፊት ለአዉሮፓ የመረጃ መከላከል ህግ እንዲጸድቅ ቀርቦ 28 አባል መንግስታት በጉዳዩ ልዩነት ስለነበራቸዉ ታግዷል። የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽነር ሆሴ ማኑዌል ባሮሶም በበኩላቸዉ አዉሮጳዉያን የግለሰብን የግል ጉዳይ ማክበርን እንደመሠረታዊ መብት ይመለከቱታል ነዉ ያሉት። የኅብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ዛሬ እና ነገ የኤኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ጉባኤ ለማካሄድ የተሰባሰቡ ሲሆን የጀርመን መራሂተ መንግስት ስልክን የመጠለፍ ወሬ ትኩረታቸዉን ወደሌላ ሳይስብ እንዳልቀረ እየተነገረ ነዉ።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሂሩት መለሰ
 Source: www.dw.de

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog