በውኃ ላይ የታነፀው ይምርሐነ ክርስቶስ የ“ወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ የ2014 ተመራጭ መካነ ቅርስ” ሆነ

ከዛጒዌ ስመ ጥር ነገሥታት አንዱ በነበሩት በንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ዘመነ መንግሥት ከተሠሩት ኪነ ሕንጻዎች አንዱ የኾነው ይምርሐነ ክርስቶስ፤ የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ የ2014 ተተኳሪ መካነ ቅርስ (2014 World Monuments Watch) ሆኖ ተመረጠ፡፡
ፈንዱ መስከረም 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ዋና ጽ/ቤቱ በሚገኝበት በኒው ዮርክ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው÷ እ.አ.አ በ2014 ዓለም በትኩረት ሊያውቃቸው፣ ሊጠብቃቸውና ለትውልድ ሊያስተላለፍላቸው ይገባል ካላቸው የ41 አገሮች ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ልዩ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚታይበት የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ አንዱ ኾኖ መመረጡ ተገልጧል፡፡
“ወርልድ ሞኑመንትስ ዎች” በተሰኘው ፕሮግራሙ ለአደጋ የተጋለጡና ዝነኛ የቱሪስት መስሕብ የኾኑ ታሪካዊ ኪነ ሕንፃዎችንና

ባህላዊ መካነ ቅርሶችን በማስተዋወቅ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በመለገሥ ዘመን ተሻጋሪ እንዲኾኑ ዓለም አቀፍ ቅስቀሳ የሚያደርገው ወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ፣ በዝርዝሩ ያካተታቸው የተመረጡ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙና በአግባቡ እንዲጠበቁ በዓለም ዙሪያ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ የዓለም ቅርሶች የፈንዱ ተጠቃሚ ሲኾኑ ከእኒህም መካከል ፈንዱ እ.ኤ.አ በ1966 ሲቋቋም የክብካቤና ድጋፍ ሥራውን የጀመረባቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደስ እንደሚገኙበት በመግለጫው ተመልክቷል።
የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ በዓለም አቀፍ ፈንዱ ተመራጭ እንዲኾን በመጠቆምና ለምርጫው የሚያግዙ መረጃዎችን በማቅረብ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ለአዲስ አድማስ የገለጸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ክብካቤና ልማት ማኅበር፤ መካነ ቅርሱ የ2014 የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ ተመራጭ መኾኑ ኪነ ሕንጻውን የበለጠ ለማስተዋወቅና ለማልማት ዕድል ይሰጣል ብሏል፡፡ ቅርሶች ዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ያበረክቱ ዘንድ ራእይ የሰነቀው ሀገር በቀል ማኅበሩን ጨምሮ በቅርስ ክብካቤ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ የሥራ ሓላፊዎችና ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የብዙኀን መገናኛና ሌሎች አካላት ጋራ በመተባበር እንንዲንቀሳቀሱም ምቹ ኹኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡
ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት በሰሜን ወሎ ወግረ ስኂን በሚባል ቦታ ሰፊና ግርማ ሞገስ ባለው የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ በውኃ ላይ እንደታነፀ የሚታመነውና ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይበት ይምርሐ ክርስቶስ÷ በአገራችን ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውን የቤተ መንግሥት ሕንጻ፣ በድንቅ ጥንታዊ ሥዕሎችና ንድፎች ያሸበረቀ ቤተ መቅደስ አሰናኝቶ የያዘ መካነ ቅርስ ነው፡፡ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች፣ ያልፈረሱና ዕድሜ ጠገብ የሰው ዐፅሞች፣ የሀገር በቀል ዕፀዋት ጥቅጥቅ ደንና ማራኪ መልክአ ምድር የሚገኙበት ነው፡፡

Source: http://www.addisadmassnews.com/
 

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog