ተሰባስበን በመጠጣት ላይ እያለን እንዳጋጣሚ አንዱ ጓደኛችን ቪያግራ ስለሚባለው የስንፈተ ወሲብ መድኃኒት አነሳን፡፡ እሱ እንደነገረን ግን የስንፈተ ወሲብ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ በሞቀ ስሜት ለመቆየት የሚያስችል እና በቅርብ ጓደኛው ከዱባይ እንዳመጣለት ነገረን፡፡ የተወሰኑት በእረፍትና በድፍረት መሀከል ሆነው እስኪ እንሞክረው ሲሉ ተስማሙ፡፡
እኔና አንዱ ጓደኛችን በድምፅ ተአቅቦ ዝም ብለን ማዳመጥ ቀጠልን፡፡ እርግጥ አልፎ አልፎ ከባለቤቴ ጋር ወሲብ ለመፈፀም ስፈልግ ስሜቴ ስለማይነቃቃ ባለቤቴ ላይ መከፋት አያለሁ፡፡ እናም እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር እንደጓደኞቼ ምን አለ ብጠቀም ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን ግን ስጋቴ ከዛ በኋላስ ምን ሁኔታ ውስጥ እገኛለሁ ብዬ ሳስብ ይጨንቀኛል፡፡ ታዲያ ለዚህ ብዬ ባለሙያዎችን ለማማከር ወደ ህክምና ብሄድ ቅብጠት ይሆንብኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ልጠቀም አልጠቀም በሚል ውዝግብ ለመውጣት ሁሉንም ለመርሳት ሞከርኩ፡፡ ነገር ግን መድኃኒቱን ከሌላ ሰው እጅ በማግኘቴ ገዝቼ አስቀምጬዋለሁ፡፡ እንደው ምን አልባት ቢያስፈልግ ብዬ፡፡ ሲል ስሙን እንዳልጠቅስ ከነማስጠንቀቂያ የነገረኝ ጓደኛዬ ያነሳልኝን ጨዋታ ተመርኩዤ በዚህና መሰል የስንፈተ ወሲብና አማራጭ መድኃኒቶች ዙሪያ ባለሙያ አነጋግሬ ይዤላችሁ ቀረብኩ፡፡
ችግሩ በአበባ ወጣቶች ላይ መንሰራፋቱን ከተለያዩ ሰዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ እናስ ህክምናው ምን መልስ አለው፡፡ ዶ/ር ድጋፌ ፀጋዬ የቆዳና የአባላዘር ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ከስንፈተ ወሲብ በመነሳት እንዲህ ያስረዱናል፡፡
በወንዶች ላይ የሚታዩት የስንፈተ ወሲብ ችግሮችን በሶስት መልኩ ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ አንደኛው የብልት መነሳት ችግር (Reactive dysfunction) ወይም የወሲብ ስንፈት እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ ሁለተኛው እርካታ ደረጃ ሳይደርስ የዘር ፈሳሽ ማውጣት (premature ejaculation) ሶስተኛው የወሲብ ስሜት አልባነት ናቸው፡፡

የመጀመሪያውን ስንመለከት የብልት መነሳት ችግር ያለባቸው ሰዎችን በብዛት እናገኛለን፡፡ በተለያየ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቢያጠቃም በተደጋጋሚ ወደ ህክምና የሚመጡት ግን ዕድሜያቸው ከስልሳ ዓመት በላይ በሆኑት ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ወጣቶችም ሪፖርት ሊያደርጉ ችለዋል፡፡
ችግሩ ከየት ይነሳል? ብለን ስንመለከት ሁለት አይነት ምክንያቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ከስነ ልቦና (Phylogenic) ጋር የተያያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኦርጋኒክ (ምክንያታዊ) የሆኑ የተለያዩ በሽታዎች በሚፈጥሩት ተፅዕኖ ይከሰታል፡፡ ዋነኛው የስንፈተ ወሲብ መንስኤ ተብሎ የሚጠቀሰው የስነ-ልቦና ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የአዕምሮ ውጥረት በሚኖርበት ጊዜ ጭንቀት እና የተለያዩ ሀሳቦች ለስንፈተ ወሲብ ያጋልጡናል፡፡ ሌላው የአካል ድካም እና መዛል ነው፡፡ ለምሳሌ አካሉ በብዙ ስራ ሲንቀሳቀስ የዋለ ሰው በግንኙነት ወቅት የብልት መነሳት፣ ስሜት ማጣት አሊያም ለወሲብ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡ ብልት እርቀት ደረጃ ሳይደርስ አስቀድሞ ጥንካሬውን የሚያጣበት ምክንያት የሀሳቦችን መደራረብ በመኖራቸው ነው፡፡ ይህን በምሳሌ ብንመለከት ከፍቅር ጓደኛው ጋር ወሲብ በሚፈፅምበት ወቅት ነጋዴ ከሆነ ስለተጋረጠበት የንግድ ችግር የመስሪያ ቤት ኃላፊ ከሆነ ስላልተሳኩ የድርጅቱ እቅዶች ካለው ኃላፊነት ጫና የተነሳ በአዕምሮው ሊመላለሱበት ይችላሉ፡፡ ይህም ጥሩ ያልሆነ ግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ግብረስጋ ግንኙነት ደግሞ በባህሪው ሙሉ ለሙሉ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው በባልና በሚስት መካከል አለመግባባት /ቅሬታ በሚኖርበት ጊዜ ተነሳሽነቱ በሁለቱም ወገን ይቀንሳል፡፡ በቀጥታ ከአዕምሮ ጋር የሚያያይዘው የግብረ ስጋ ግንኙነት ስነ-ልቦናና አካላዊ ዝግጁነት ጅማሪ አይምሮ ውስጥ በሚፈጠር ኬሚካሎች አማካይነት ነው፡፡ የአንድሮጂን ኬሚካል መመረት ወንዶች ላይ ብዛት የደም ፍሰቱ ወደ ብልት እንዲሆን በማድረግ ብልት እንዲነሳ ያደርጋል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች ይህን ኬሚካላዊ የዝግጁነት ቅመም እንዳይፈጠር ስለሚያደርጉ የፓርኖግራፊ ፊልሞች በሚፈጥሩት፣ በአደጋ (ግጭት) ጫና፣ በሃዘን፣ በድካም መካከል ስንፈተ ወሲብ እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም ነው ብልት የመነሳት ችግር የሚያጋጥመው፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ኦርጋኒክ የሚባለው ሲሆን የተለያዩ ህመሞችን ተከትሎ የሚመጣ የወሲብ ችግር ሲሆን ስኳር፣ ደም ግፊትና የአባላዘር በሽታዎች ሲያጠቁን ነው፡፡ ሌላው የተለያዩ አደገኛ መድኃኒቶች አልኮልና ጫት የደም ዝውውርን የሚቀንሱ ናቸው፡፡ በግንኙነት ወቅት ብልት እንዲነሳ ካስፈለገ ከፍተኛ የደም ዝውውር ሊኖር ይገባል፡፡ በቂ የሆነ የነርቭ መነቃቃትም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚያስከትሉት ጫና ደግሞ በወሲብ የመነቃቃትና ትክክለኛውን ኡደት ጠብቆ በሚጠበቀው ደረጃ እርካታ ላይ ለመድረስ እንዳይችሉ እንቅፋት ይሆናል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉን ህክምናዊ መፍትሄዎች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ስንመለከት በቅድሚያ ወሲባዊ ህይወት እንደ ምስጢር በየሰው አዕምሮ ውስጥ በመቀበሩ ችግሮችን አውጥቶ ከህክምና ባለሙያዎች እና ከትዳር አጋር ወይም ፍቅረኛ ጋር ለመወያየት አለመቻል በራሱ ችግሩን የሚያባብሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከህክምናው ጋር የተገናኙትም በትክክል ህክምና ተከታትለው ሲያጠናቅቁ አይታዩም፡፡ በመሆኑም በቀላሉ መፍትሄ ላያገኙ ከሚችሉበት አጋጣሚ በመራቅ ለተለያዩ አላሰፈላጊ የጊዜና ገንዘብ ብክነቶች ይዳረጋሉ፡፡
በመሆኑም መፍትሄው የመጀመሪያው እርምጃ የችግሩን መነሻ ምክንያትን ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ እንደመንስኤው የተለያዩ ህክምናዎች እንዲሰጡበት ያደርጋል፡፡ ከስነ-ልቦና ጋር የተያያዘ ከሆነ ያለመድኃኒት ሊስተካከል ይችላል፡፡ ያለውን ችግር ማለትም አካላዊና አዕምሮአዊ ሁኔታ የስነ-ልቦና ድጋፍ በማግኘት በማስተካከል ሊቀረፍ ይችላል፡፡ ከተለያዩ ህመሞች የሚነሳው የስንፈተ ወሲብ ችግር ከመቆጣጠርና ከመከላከል ባሻገር መድኃኒቶችን ለደም የሚገባውን የወሲብ ስሜት መጠበቅ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ፡፡ በዚህ ውስጥ አልፈን መፍትሄ ካልተገኘ የመጨረሻው አማራጭ ረዳት መድኃኒቶችን ማካተት ይሆናል፡፡
እነዚህ መድኃኒቶች ያላቸው ጥቅም ምንድን ነው ካልን የደም ዝውውር በመጨመር ነርቮች እንዲነቃቁ የወንዱ ብልት አካባቢ ያሉት ጡንቻዎች እንዲኮማተሩ እና ብልት እንዲጠነክር የሚያደርጉ ናቸው፡፡ መድኃኒቱም በህክምና ባለሙያ ትዕዛዝ መሰረት በጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም አይነትና መጠኑ ሊያውቅ የሚችለው በህክምናው ዘርፍ በቂ ትምህርትና ልምድ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ተያይዘው ለሚመጡ ተጓዳኝ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ተጠንተው ቅድመ እና ድህረ ጥንቃቄ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ችግሩ እንዲቀረፍ 50 በመቶ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ከችግሩ አይነትና መጠን ተነስተን ነው መድኃኒቶቹን የምናዘው፡፡
መድኃኒቶች ያሏቸውን ጥቅም ያህል ብዙ ጉዳቶችንም ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ነው የባለሙያ ድጋፍ አስፈላጊነት ሁኔታዎችን በማገነዛብ መድኃኒቶችን ማዘዝ ውጤታቸውንም መከታተል ከተቻለ መድኃኒቱ ያለምንም ጉዳት የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያስመዘግብ ይረዳዋል፡፡
መድኃኒቱ መታዘዝ ያለበትን ወቅት በተመለከተ ምክንያቱ ታውቆ አማራጭ መፍትሄዎች ታይተው ግድ የሚሉ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ነው፡፡ የመድኃኒቱ መጠን እና አይነት መቼስ መውሰድ አለበት? እነማንናቸው መድኃኒቱን መውሰድ የሚችሉት? እነማንስ መድኃኒቱንሲወስዱ ችግሮች ይገጥማቸዋል? የሚለውን የሚወስነው ባለሙያው ነው፡፡
ሰዎች ከተለያዩ ምንጮች ካገኟቸው መረጃዎች ተነስተው መድኃኒቶችን ያለህክምና ትዕዛዝ ይወስዳሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሄ ሊሰጥ ወደሚችለው ባለሙያ ለመሄድ ያለው ተነሳሽነት በጣም ዝቅተኛ መሆን፣ የወሲብ ምስጢራዊነት እሳቤ፣ የመድኃኒቶቹን የጎንዮሽ ችግር ያለመረዳት፤ የጓደኛና የተለያዩ የወሲብ ትዕይንቶች ከሚያስከትሉት ጫና የተነሳ ነው፡፡ ችግሩ ሳይኖር መድኃኒቶችን አፈላልጎ መጠቀም የመቻል አቅምና ድፍረት በተጨማሪ ህገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር መኖሩ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
ለምሳሌ ቪያግራ ተሰኘውን መድኃኒት በተለያየ መልኩ ማግኘት የቻሉ ሰዎች ዝም ብለው ቢጠቀሙበት ምን ያስከትላል ስንል የልብ ድካም ያለባቸው (አርቴፊሻል መሳሪያዎች በልባቸው የተገጠመላቸው ሰዎች) ችግር ይገጠማቸዋል፡፡ መድኃኒቶቹ በዚህ ሁኔታ ከጥቅም ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡
በተጨማሪም ከልክ ያለፈ የብልት መነቃቃት ሳቢያ ብልት ቆሞ ላይመለስ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህም Persistence stimulation ያስከትላል፡፡ ሌላው በግንኙነት ወቅት ብልት በጣም ከመወጣጠሩ የተነሳ የብልት ዘንግ ስብራት ሊያጋጥም የሚችላቸው ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ አንድም ጊዜያዊ ከፍተኛ ህመም፡፡ በተጨማሪም የልብ ስራን የማዛባት ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡
የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶቹን ማግኘት ስለተቻለ ብቻ መጠቀሙ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ብዙ ጊዜ መድኃኒቱ እንደ ችግሩ ሁኔታ ታይቶ በቀን አንዴ ግንኙነት ከማድረጊያ ጊዜ አንድ ሰዓት ቀድሞ እንዲወሰድ የሚታዘዝ ሲሆን በተደጋጋሚ እንዲወሰድ አይመከርም፡፡
መድኃኒቱን ደጋግሞ መውሰድ አስቀድመን የጠቀስናቸውን ችግሮችን ማባባስ ያስከትላል፡፡ በተለምዶ የወንዶች ብልት ከተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ ቦታው ይመለሳል፡፡ ለረጅም ሰዓት ተነስቶ በሚቆይበት ወቅት እጅግ በጣም ከፍተኛ ህመም አለው፡፡ መልሶ ግንኙነት ማድረግ በሚያስፈልግበት ጊዜም ሊያስቸግር ይችላል፡፡
እንደ ቪያግራ ያሉ መድኃኒቶችን መጠቀም የጀመረ ሰው የጥገኝነት ባህሪ ስለሚዋሃደው ያለው በራስ መተማመን ይቀንሳል፡፡ ያለመድኃኒቱ በተፈጥሮአዊ መንገድ ለወሲብ መዘጋጀት እና መደሰትም ያቅተዋል፡፡ የቪያግራ መድኃኒት በኪኒን መልክ የሚሰጥ ሲሆን አልፎም በመርፌ መልክ ወንድነትን የሚያላብሰው የቴስቴስትሮን ሆርሞን በጊዜ ሂደት ሲቀንስ ቅመም አመንጭውን ክፍል ለማነቃቃት (መጠኑን ለመጨመር) የሚያስችል በሳምንት አንድ መርፌ ይሰጣል፡፡ ስለሆነም ስንፈተ ወሲብ ያስከተለው የቴስቴስትሮን ማነስ፣ የስነ-ልቦና ጫና አካላዊ ድካም ወዘተ… መንስኤዎች ውስጥ የትኛው እንደሆነ ታውቆ መድኃኒቶች ይመረጣሉ፡፡
አብዛኛው ስንፈተ ወሲብ ችግሮች ባህሪን ከማስተካከል፣ ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እና ምክር በመስጠት ያለመድኃኒት ሊታከሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ ህክምና ቦታ መጥተው ፈራ ተባ እያሉ የመናገር ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ ይህ ተወግዶ ግልፅነት ከዳበረ ችግሩ እንዲቀረፍ ይረዳል፡፡ በወጣቶች በኩል ለዚህ ችግር የሚጋለጡበት ዋነኛ ምክንያት በሱስ መጠመድ ሲሆን በተለይም ለረጅም ጊዜ ጫት መቃም እና በብዛት አልኮል የሚወስዱ ከሆነ ለስንፈተ ወሲብ ይጋለጣሉ፡፡ ከጋብቻ በፊት የሚኖር ከግብረ ስጋ ግንኙነት ለስንፈተ ወሲብ ያጋልጣል፡፡ በደንብ ሳይተዋወቁ ስሜታዊ ወሲባዊ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ሰዎች በሚያድርባቸው ስነ-ልቦና ጫና የስንፈተ ወሲብ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡
እኛ አገር ባይኖርም በባለትዳሮች መሀከል የሚደረግ የወሲብ ህክምና በተለያዩ ሀገሮች የሚሰጥ ሲሆን ከትዳር አጋር ጋር በሚያጋጥም የወሲብ አለመጣጣም ችግሮችን በማጥናት መፍትሄ ማስቀመጥ የሚቻልበት ሂደት ነው፡፡ በወሲብ ህይወት ውስጥ ዝግጁነት እና ግልፅነት ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡ ስለ ወሲብ ከትዳር አጋር (ፍቅረኛ) ጋር በግልፅ በማውራት ለችግሮቹ መፍትሄ ለመፈለግ ይረዳል፡፡ በዚህ ሳቢያ የሚደርስ የትዳር መፍረሶችን መታደግ ይቻላል፡፡ ተገቢውን ህክምና ማግኘት እና በተለይም ቤተሰባዊ መረዳዳት እና በወሲብ ወቅት ማዘጋጀት፣ እራስን የተረጋጋ፣ ፍቅር የተሞላበት እና መተማመን የሰፈነበት ወሲብ ሙሉ ደስታን ያጎናፅፋል፡፡
ቪያግራን ወንዶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ሲጠቀሙበት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም የታወቀ ሲሆን ይህ መድኃኒት ለሴቶች ጥቅም ስለማይኖረው በድፍረት እና ባለማወቅ የወሲብ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለው ሴቶች እንዳይቀጠሙበት እናስጠነቅቃለን፡፡
መድኃኒቶች ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች ሲገቡ ጥራታቸው ያልተፈተነ፣ የማዳን አቅማቸው፣ የጎንዮሽ ጉዳታቸው፣ የአወሳሰድ መጠናቸውና ልዩ ጥቅም የሚያስገኝባቸው ችግራዊ መንስኤዎች ስለማይታወቁ ያለሐኪም ትዕዛዝ መውሰዱ ለከፋ ችግር ያጋልጣሉና የጥንቃቄ እርምጃው እየተስተዋለ ሊሆን ይገባዋል፡፡
Source: http://www.tenaadam.com/
አሜሪካዊ እንደራሴና የሥለላ ጉዳይ አዋቂ ፔተ ሆክስትራን የሚያስደንቀዉ ግን የአሜሪካ ሰላዮች የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥትን ስልክን መጥለፋቸዉ አይደለም።የነፍሬድሪሽ ቁጣና ብስጭት እንጂ።ሆክስትራ እንደሚሉት ካስደነቀ-የሚያስደንቀዉ የጀርመን
መሪ ሥልክ መጠለፉን ፍሬድሪሽ የሚመሩት የጀርመን የስለላ ድርጅት አለማወቁ ነዉ። ለካሳትሮ፥ ለብሬዥነቭ፥ ለማኦ፥ ለ ደጎል፥ ለንጎ በርግጥ አዲስ አልነበረም። አይደለምም።የኤንርኮ ፔና ኔቶ ኢሜል መጠለፍ- ጉድ አሰኝቶ ነበር።የዲልማ ሮሴፍ-ኢሜል መጠለፍ-አስደንቆ ነበር።የሜርክል ሥልክ መጠለፍስ? ጉዱን ጉድ ዘለቀዉ-እንበል ይሆን።የስላላዉ ቅሌት መነሻ፥ዳራዉ ማጣቃሻ፥ የፖለቲካዉ እድምታዉ መድረሻችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
ሚዚያ ሃያ-አንድ 1943 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ፈረንሳይን ከናዚ ጀርመኖች አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት የሚዋጋዉ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሻርል ደጎል የነፃዋ ፈረንሳይ ባሕር ሐይል ጦርን ለመጎብኘት ከተጠጉባት ብሪታንያ በብሪታንያ አዉሮፕላን ተሳፈሩ።ቆፍጣናዉ፥ ቁጡዉ፥ እልሐኛዉ ረጅሙ ጄኔራል ከትንሿ አዉሮፕላን እንደተሳፈሩ አብራሪዉ (ፓይለቱ) አዉሮፕላንኗን እንደማስነሳት ትንሽ አንገጫገጨና ወዲዚያዉ አቆማት።ጉዞዉ ተዘረዘ።
አዉሮፕላንኗ ስትፈተሽ የሞተሯ አካል በአሲድ መበላሸቱ ታወቀ።አሲዱን አዉሮፕላንዋ አካል ላይ የረጨዉ ወገን ማንነት-እስካሁን ሚስጥር ነዉ።ጄኔራሉ ግን ያኔዉኑ «የብሪታንያ ሰላዮች ሻጥር» ለማለት አላመነቱም።የአዉሮጳ እብሪተኞች የለኮሱት ጦርነት ዓለምን በሚያነድበት በዚያ ዘመን ወዳጅን ከጠላት መለየቱ-ከባድ ነበር።በዚሕም ሰበብ ደ ጎል እንደጠረጠሩት ብሪታንያዎች አድርገዉት ከነበር-ብዙዎችን ብዙም አላስደነቀም ነበር።
ከብዙ አመታት በሕዋላ የደጎልን ቤተ-መንግሥት የተረኩቡት ፕሬዝዳት ኒኮላ ሳርኮዚ ከጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት ከወይዘሮ አንጌላ ሜርክል ጋር የነበራቸዉ ግንኙነት ከመሪዎች-ወዳጅነትም ጠንከር፥ ጠለቅ ያለ-ነበር ይባላል።ሳርኮዚ ከሜርክል ጋር ሥላላቸዉ ግንኙነት ሥለሚያደርጉት ዉይይት ሲጠየቁ፥«ሁሌ እንገናኛለን፥ በስልክ፥ እንነጋገር፥ ኤስ ኤም ኤስ እንለዋወጣለንም» እያሉ የግንኙነት ዉይይታቸዉ ደረጃ ዘርዝረዉ ነበር።

የሜርክል መልዕክት ከሳርኮዚ አይን-ጆሮ በሚደርስበት ፍጥነት ከአሜሪካ ሰላዮች ኮምፒዉተር ላይ ይዘረገፍ ነበር።ይሕን በርግጥ ሳርኮዚም፥ ሜርክልም ከኛ እኩል ያወቁት ሰሞኑን ነዉ።NSA በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የአሜሪካ ብሔራዊ የሥለላ ድርጅት ባልደረባ የነበሩት ቶማስ ድራክ እንደሚሉት ሜርክልን መሠለል ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲን መጣስ ነዉ።

«ይሕ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲን ክፉኛ መጣስ ነዉ።ይሕ ለመራሒተ-መንግሥት ሜርክል የግል ጉዳይ ነዉ።የግላቸዉ ተንቀሳቃሽ ሥልክ ነዉ።(ያን መጥለፍ) ለምን አስፈለገ።ከእዉነኛ ጠላትሕ ጋር በምታደርገዉ ዉጊያ የቅርብ ተባባሪሕን?»
ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፥ ዓለም አቀፍ ሕግ በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት ነበር።ዛሬም አለ።አንዴም ግን ተከብሮ አያዉቅም።ሕግ፥ ደንብ፥ ሥምምነቱን የሚጥሰዉ ደግሞ ሕግ-ደንቡን ካወጣዉ፥ አስከብረዋለሁ ከሚለዉ ሐያል ዓለም ሌላ ማንም አይደለም።

በቀዝቃዉ ጦርነት ወቅት ልክ እንደ ዓለም አቀፉ ሕግ ደንብ ሁሉ የሞስኮ፥ ቤጂንግ ተባባሪዎች፥ የለንደን-ዋሽግተን፥የቦን ፓሪስ ተሻራኪዎች ጎራ ለይተዉ አንዱ የሌላዉን ሚስጥር ማጭለጉ የፖለቲካዉ ፈሊጥ፥ የስለላዉ ወግ ነበር።

የሐገር መሪዎችን እንቅስቃሴ መከታተል አይደለም መግደል ማስገደልም የፖለቲካ መርሕን የማጠናከር፥ ርዕዮተ-ዓለምን የማዳን-ማስፋፋት ሥልት አካል ነበር።የአሜሪካዉ ማዕከላዊ የሥለላ ድርጅት CIA ሹም ኮሎኔል ጄ ሲ ኪንግ የኩባዉን ኮሚንስታዊ መሪ ፊደል ካስትሮ-ከማስገደል ሌላ ሌላ አመራጭ እንደለሌ የጠቆሙት በ1959 ነበር።

ያኔ ዓለም አቀፍ ማሕበር ዲፕሎማሲ፥ ሕግም ነበር።ዲፕሎማሲ ሕግ፥ ደንቡ የሚረቀቅ፥ የሚወሰን የሚበየነዉ ደግሞ ከኒዮርክ ነበር፥ ከዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ።የአሜሪካዊ ማዕከላዊ የሥለላ ድርጅት CIA ካስትሮን ለማስገደል ስድስት መቶ ሰላሳ-ስምንት ጊዜ ያደረገዉ ወይም አድርጓል የተባለዉ ሙከራ የብዙ መፅሐፍት፥ የዝነኛ ፊልም ርዕሥም ሆኗል።

አያቱላሆች የቴሕራንን ቤተ-መንግሥት ከተቆጣጠሩበት ከ1979 ጀምሮ ኢራን የእስራኤልም፥ የአሜሪካኖችም አሜሪካኖችን የሚመሩት የምዕራቡ ዓለምም ቀንደኛ ጠላት ናት።በሕዝብ የተመረጡት የኢራን ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሞስዳቅሕን በ1953 ከስልጣን ያስወገደዉ ማን ነበር? ፓትሪስ ሉምባ እንዴት-እና ማን ገደላቸዉ።ራፋኤል ሊኒዳስ ትሩሔሎስ፥ ንጎ ዲንሕ ዲየምንስ?
ጥያቄዉ-ጥያቄ ይወልዳል እንጂ ማብቂያ የለዉም።ዓለምን የሚመራዉ ግን ዓለም አቀፉ ሕግ ዲፕሎማሲ ሳይሆን የሐያላን ፍላጎትና ፍቃድ መሆኑ ሐቅ ነዉ።የሐያላኑን ፍላጎት ለማስከበር ደግሞ በግልፅ የሚታወቀዉ ሐያላኑ ወዳጅ ከሚሉት ጋር መተባበር መሻረክ መወዳጀታቸዉ ነበር።እስከ 2007 ድረስ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የስለላ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር የነበሩት ፔተ ሆክስትራ እንደሚሉት ግን በስለላዉ ዓለም ከወዳጅም-መሐል ተጠርጣሪ ወዳጅ አለ።

«ይሕ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል።በስለላዉ ዓለም ፈረንሳዮች፥ ጀርመኖች፥ እስራኤሎች አሜሪካኖች ሁላችንም ጥሩ ወዳጆች ነን።ግን አንዳችን ሌላችንን የምንሠልልበት ጊዜ ሊኖርም ይችላል-የሚል መግባባት ያለ ይመስለኛል።ይሕ (በሰላዮች ዘንድ) በጣም በጣም የታወቀ ነዉ።»

ኮሚንስቶች የሐቫና፥ የሳንዲያጎ፥ የማናጉዋ የሌሎችንም የደቡብ አሜሪካ ሐገራት አብያተ-መንግሥታትን ሲቆጣጠሩ ወይም ለመቆጣጠር ሲያሰጉ የዩናይትድ ስቴትስዋ የቅርብ ጎረቤት፥ ታማኝ፥ ታዛዥነቷን አጓድላ አታዉቅም።ሜክሲኮ።

ከቀዝቃዛዉ ጦርነት በሕዋላ እነ-ሑጎ ሻቬዝ አሜሪካኖችን የሚቃወም ግንባር ለመፍጠር ሲፍጨረጨሩም ያቺ-የአሜሪካ የቅርብ ጎረቤት በታማኝ ታዛዥነቷ እንደፀናች ነበር።ነዉም።ኤንሪክ ፔና ኒቶ ለፕሬዝዳትነት ሲወዳደሩ-ሲመረጡም እንደ ብዙ ቀዳሚዎቻቸዉ ሁሉ ለሐያል፥ ሐብታም፥ ታላቅ ጎረቤታቸዉ ታማኝ ታዥነታቸዉን እንደጠበቁ ነዉ።

በእጩነት ከተመዘገቡ ጀምሮ በምርጫዉ ካሸነፉ-ለሚንስትርነት የሚሾሙ የሚሽሩትን ፖለቲከኛ ስብዕና ማንነት፥ የሚዘረዝር፥ የምርጫ ዘመቻቸዉን ሥልት የሚያትት መልዕክት ለወዳጅ ተከታዮቻቸዉ ኢሜይል ይፅፋሉ። የNSA ሰላዮች ዋሽግተን ቁጭ ብለዉ የሜክሲኮዉን ፕሬዝዳት ኢሜይል ከፕሬዝዳንቱ ደጋፊ፥ተከታዮች እኩል ያነቡ ነበር።የብራዚሏ ፕሬዝዳት የወይዘሮ ዲልማ ሮሴፍ ኢሜዬልም-እንደዚያዉ ነዉ።

አሜሪካዊዉ ሠላይ ኤድዋርድ ስኖደን ሐገር መስሪያ ቤቱን ክዶ ከኮበለለ ወዲሕ የማይሰማ ጉድ የለም።አንዳድ ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የሶቬት ሕብረት ኮሚንስቶች በስታሊን ዘመን የሶቬት ሕብረት ሕዝብ ከሚሠልሉት በላይ የአሜሪካ መንግሥት አሜሪካዉያንን ይሰልላል።ለአሜሪካ ሕዝብ ያልራራ ሥርዓት የፈረንሳይ ኩባንያዮችን፥ የስጳኝ ፖለቲከኞችን፥ የዓለምን ሕዝብ የሜክሲኮ፥ የብራዚል፥ የሌሎች ከሰላሳ በላይ መሪዎችን ቢሰልል-በርግጥ ሊያስደንቅ አይገባም።

ያምሆኖ የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት የሥልክ መልዕክት መጠለፉን ከአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት እስከ ሩሲያ መሪዎች ተቃዉመዋል።የጀርመን ፖለቲከኞች የሜርክል ደጋፊም ሆኑ ተቃዋሚዎችም እኩል አዉግዘዉታል።

«እንደሚመስለኝ ይሕ በጀርመን-አሜሪካኖችን ግንኙነት ያለዉን መተማመን ክፉኛ የሚጎዳ ነዉ።መተማመኑ ዳግም ሊገነባ የሚችለዉ እዉነታዉ በግልፅ ወጥቶ ማየን ከቻልን በኋላ ነዉ።

ይላሉ፥-የዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ የSPD የምክር ቤት እንደራሴዎች አስተባባሪ ቶማስ ኦፐርማን ።ሥለ ጀርመን እና ጀርመንን የሚመለከቱ መረጃዎችን የመሰብሰብ መከታተሉ ሐላፊነት የጀርመን የሥለላ ድርጅት ነዉ።ቡንደስ ናሕሪሽተን ዲንስት።BND በጀርመንኛ ምሕፃሩ። የስለላዉን ድርጅት በበላይነት የሚያስተዳድርና የሚመራዉ ደግሞ የጀርመን ፌደራዊ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ነዉ።

የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ሐንስ ፔተር ፍሬድሪሽ ግን የመሪያቸዉን መሰለል እንደማንኛዉም ሰዉ ከመገናኛ ዘዴዎች የሰሙ ያክል ነዉ-የተቆጡት።

«ከአሜሪካኖች ጋር በዚሕ ሁኔታ አንሰራም።መተማመኑ ተበላሽቷል።እና እንደሚመስለኝ የተበላሸዉን መተማመን ለመጠገን ሁነኛ እርምጃ መወሰድ አለበት።»

አሜሪካዊ እንደራሴና የሥለላ ጉዳይ አዋቂ ፔተ ሆክስትራን የሚያስደንቀዉ ግን የአሜሪካ ሰላዮች የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥትን ስልክን መጥለፋቸዉ አይደለም።የነፍሬድሪሽ ቁጣና ብስጭት እንጂ።ሆክስትራ እንደሚሉት ካስደነቀ-የሚያስደንቀዉ የጀርመን መሪ ሥልክ መጠለፉን ፍሬድሪሽ የሚመሩት የጀርመን የስለላ ድርጅት አለማወቁ ነዉ።

«የዋሕነት ይመስለኛል።የጀርመን መንግሥት (ባለሥልጣናት) በወዳጆቻቸዉ ሊሰለሉ እንደሚችሉ ማወቅ ነበረባቸዉ።ነገሩ ከተፈፀመ አስደናቂዉ ነገር የሚመስለኝ፥ (ሥለላዉን) ለማስቆም የጀርመን የስለላ ማሕበረሰብ አስፈላጊዉ አፀፋ-እርምጃ አለመዉሰዱ ነዉ።»
የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት ስልክ መጠለፉ-መሰላላቸዉም እርግጥ ነዉ።ሜርክል መሰለላቸዉን ፕሬዝዳት ባራክ ኦቦማ ያዉቃሉ-አያዉቁም እያነጋገረ ነዉ።ካወቁ ከመቼ ጀምሮ የሚለዉም ያጠያይቃል። እራሳቸዉ ሜርክል እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ፍራንሷ ኦሎንድ የአዉሮጳ ሕብረት ወክለዉ ለኦባማ አቤቱታ ያቀርባሉ። ወደ አንድ ሺሕ የተገመቱ አሜሪካኖች በመንግሥታቸዉ መሠለላቸዉን በአደባባይ ሠልፍ አዉግዘዋል።አቤቱታ፥ ተቃዉሞ፥ ዉግዘት፥ ሰልፉ ምናልባት ይቀጥል ይሆናል፥ መሳለል-መጠላለፉ ያስቆመዋል ባይ ግን የለም።ምክንያት፥-ድሮ እንዲያ ነበር፥ ዛሬ እንዲያ ነዉ።ነገም።በዚሕ ዝግጅት ላይ ያላችሁን አስተያየት ላኩል። ማሕደረ ዜና ቢቃኘዉ ጥሩ ነዉ ብላችሁ የምትገምቱትን ወቅታዊ፥ ብሔራዊ፥ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ በተለመደዉ አድራሻችን ጠቁሙን።ለዛሬዉ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰመን።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ
Source: www.dw.de
የቀድሞ አምባሳደር፤ ዘውዴ ረታ፤ ቫቲካንን ከኃላፊነት ነጻ ለማድረግ ስላደረጉት ሙከራ
ኪዳኔ ዓለማየሁ
መግቢያ፤
በቅርቡ፤ አምባሳደር ዘውዴ ረታ የደረሱት፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” መጽሐፍ(1)፤ በሰሜን አሜሪካ፤ በልዩ ልዩ
ከተሞች እየተሸጠ በመሆኑ፤ አንድ ወዳጄ፤ ለኔም ልኮልኝ አንብቤዋለሁ። ይህን መጣጥፍ የማቀርበው ግን፤ ስለ መጽሓፉ
በአጠቃላይ ለመተቸት ሳይሆን፤ በተለይ ከገጽ 295 እስከ 314፤ “የቫቲካን አቋም በኢትዮጵያ ጉዳይ” በተሰኘው ምእራፍ፤
የቫቲካኑ ካሕን የፋሺሽቱን ጦር ሲባርኩ
የቀድሞ አምባሳደሩ፤ ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመችው ግፍና የጦር ወንጀል ሁሉ ቫቲካን ተጠያቂ አይደለችም
ያሉት፤ ከሐቅ የራቀ፤ የውድ ሐገራችንን፤ የኢትዮጵያን ክብርና ፍትሕ የሚያጓድል በመሆኑ፤ በማስረጃ የተደገፈ እውነት
ለማቅረብ ነው። በመጽሐፉ የቀረቡትን ጉድለቶች እራሳቸው በጽሑፍ እንዲያስተካክሉ፤ በኢ-ሜይልና በግልጽ ደብዳቤ ልዩ
ልዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች ቢቀርቡላቸውም፤ ለማስተካከል ፈቃደኛ ሆነው ስላልተገኙ፤ ይህ ጽሑፍ በይፋ እንዲወጣ
ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ከዚህ በመቀጠል፤ (ሀ) አምባሳደሩ የሰነዘሯቸውን ዋና ዋና ነጥቦች፤ (ለ) ኢጣልያ፤
በቫቲካን ተደግፋ፤ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ፈጸመችው የጦር ወንጀል፤ (ሐ) ስለ የቫቲካኑ ፖፕ ፓየስ 11ኛና የሙሶሊኒ ሕብረትና
ሚና፤ (መ) በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተፈጸመው የጦር ወንጀል ሐገራችን ስላጣችው ፍትሐዊ ውጤት፤ (ሠ) ሰሞኑን (August 11,
2012) የቫቲካን ተወካይ በተሳተፉበት፤ ለፋሺሽቱ መሪ፤ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ አፊሌ በምትሰኝ ከተማ ስለ ተቋቋመው መካነ-
መቃብርና መናፈሻ፤ (ረ) ኢትዮጵያ ለደረሰባት እልቂትና ውድመት ተገቢ የሆነ መካሻ እንድታገኝ በመታገል ላይ ስላለው፤ ..........
(ሙሉውን ለማንበብ ከታች ያለውን ይጫኑ)
የቅሪተ አፅም እድሜ መለክያዉ እንዴት ነዉ፤ ረጅም እድሜ እንዳለዉ የሚነገረዉ ቅሪተ አፅምስ መገኛ ቦታዉ እንዴት ይታወቃል? ከመቶ ሽ በላይ እድሜ ያላቸዉን ቅሪተ አፅሞች እድሜ መለክያ ዘዴ እጅግ ቀላሉ ነዉ ያሉን ዶክተር ብርሃኔ አስፋዉ ሉሲ «ድንቅነሽ» ስትገኝ ከነበሩ ተመራማሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
በዓለም ዉስጥ እጅግ ግዙፍ እድሜ ካላቸዉ አስረ አንድ ቅሪተ አፅሞች መካከል ዘጠኙ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘታቸው ይነገራል ። በምስራቅ ጎጃም ማችክል ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አድማጫችን አቶ አማኑኤል ከተማ እባካችሁ፤ ግዙፍ እድሜ እንዳላቸዉ የሚነገርላቸዉ ቅሪተ አፅሞች መገኛ ቦታ እንዴት ይታወቃል? የቅሪተ አፅሙ እድሜስ እንዴት ነዉ የሚለካዉ ብለዉ የላኩልንን ጥያቄ ይዘን በዛሪዉ ዝግጅታችን መልስ የሚሰጡንን ባለሞያ ጋብዘናል።
አርዲ የሚል መጠርያን ያገኘችዉና በአዋሽ ሸለቆ አካባቢ የዛሪ አስራ አንድ ዓመት ግድም የተገኘችዉ የሴት ቅሪት አፅም የዛሪ ሃያ አንድ ዓመት ግድም ስለ ሰዉ ልጅ አመጣጥ ታሪክ የነበረዉን
እምነት ማስለወጡን የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች በወቅቱ ተናግረዋል፤ አርዲ ስትገኝ። እርዲ እንደ ሉሲ ሙሉ በሙሉ አፅሟ ባይገኝም ሉሲን ግን አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዓመት እንደ ሚበልጥ ነዉ የተነገረዉ፤ ግን የቅሪተ አጽም እድሜ መለክያዉ እንዴትይሆን? በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ቋሚ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ብርሃኔ አስፋዉ እንደሚሉት፤
ከመቶ ሽ በላይ እድሜ ያላቸዉን ቅሪተ አፅሞች እድሜ መለክያ ዘዴ በተለይ እኛ እና በምስራቅ አፍሪቃ አካባቢ የምንገኝ ተመራማሪዎች የምንጠቀምበት የስሌት ዘዴ ነዉ ሲሉ ዶክተር ብርሃኔ ያስረዳሉ።
በሳይንሳዊ መጣሪያዉ Ardipithecus ramidus የተባለዉ የአርዲ ቅሪተ አጽም ከቺንፓንዚ መሰልነት ዘር ወጣ ያለ ትክክለኛ የሰዉ ዘር ሃረግ ግንድ ላይ ያለ ነዉ ተብሎአል፤ በተመራማሪዎች ። ምንም እንኻ ቅሪተ አፅሙ የዛሪ 21 ዓመት ቢገኝም የምርምሩ ስራ በደንብ ከስር መሰረቱ ሲካሄድ እና ግኝቱ ለዓለም ህዝብ ይፋ እስኪ ሆን 17 ዓመታትን መፍጀቱ ተገልጾአል።
ግን ይህ እድሜ ጠገብ የሆነ ቅሪተ አጽም መገኛ ቦታዉ በምን ይሆን የሚታወቅ ? የሉሲ ቅሪተ አጽም ሲገኝ በምርምሩ ስራ ተካፋይ የነበሩት መካከል አንዱ የነበሩት ዶክተር ብርሃኔ ብርሃኔ አስፋዉ፤ ኢትዮጵያ በስነ ምድር ጥናት እጅግ ከፍተኛ እርምጃን እያሳየች መምጣትዋን የገለፀዉ ፤ በተለይ የጀርመን ተመራማሪዎች ጋር የትብብር ስራ መኖሩን ተናግረዋል። ዶክተር ብርሃኔ አስፋዉ ለሰጡን ቃለ ምልልስ እያመሰገንን ሙሉዉን ቅንብር እንዲያደምጡ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ
ሂሩት መለሰ
Source: www.dw.de

የጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል የእጅ ስልክ በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የስለላ ተቋም ተጠልፏል የሚለዉ ዜና እያነጋገረ ነዉ። ዩናይትድ ስቴትስ ድርጊቱን እንዳልፈፀመች በመጥቀስ አስተባብላለች። ጉዳዩ በአውሮጳ መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ጀርመን የመራሂተ መንግስቷ ስልክ ሳይሰለል አይቀርም በሚል በበርሊን የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደርን ዛሬ ለማነጋገር መጥራቷ ተዘገበ። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ በጀርመን ለአሜሪካኑ አምባሳደር ጆን ኤመርሰን በዚህ ረገድ የጀርመንን ግልጽ አቋም እንደሚያቀርቡም ተገልጿል። የጀርመን መገናኛ ብዙሃን የአሜሪካን የስለላ ተቋም NSA የመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን የእጅ ስልክ ሳይጠለፍ አልቀረም የሚል መረጃ ይፋ አድርገዋል። ዋሽንግተን ግን አስተባብላለች። ይህ ከተሰማ በኋላም ሜርክል ራሳቸዉ ለፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ስልክ በመደወል የተባለዉ እዉነት ከሆነ ፍፁም ተቀባይነት የለዉም ማለታቸዉን ቃል አቀባያቸዉ ሽቴፈን ዛይበርት ገልጸዋል። የመከላከያ ሚኒስትር ቶማስ ደሚዚየር በበኩላቸዉ፤

«የሰማነዉ እዉነት መሆኑ ከተረጋገጠ በጣም መጥፎ ነዉ። አሜሪካዉያን እዉነተኛ ጓደኞቻችንነበሩ አሁንም ናቸዉ፤ ሆኖም እንዲህ ሊቀጥል አይችልም።»
ኋይትሃዉስ ኦባማ ትናንት ከሜርክል ጋ ባደረጉት የስልክ ዉይይት የአሜሪካን የስለላ ተቋም እሳቸዉን እንደማይሰልል ማረጋገጣቸዉን ቢገልጽም ከዚህ ቀደም ስለመደረጉ ያለዉ የለም። የኋይት ሃዉስ ቃል አቀባይ ኤይ ካርኔ፤
«እኔ ልገልጽ የምንችለዉ ፕሬዝደንቱ ዩናይትድ ስቴትስ መራሂተ መንግስቷን በወቅቱ እንደማትሰልል፤ ወደፊትም እንደማትሰልል እንዳረጋገጡላቸዉ ነዉ። ዩናይትድ ስቴትስ ከጀርመን ጋ ሰፊ የጸጥታ ችግሮችን በተመለከተ ላለን የቀረበ ትብብር ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች።»
ስለሜርክል ሞባይል መጠለፍ የተሰማዉ የNSA በቀድሞዉ ባልደረባ ኤድዋርድ ስኖዉደን ጉዳዩን አጋልጦ በርካቶች መራሂተ መንግስቷ ነገሩን ያደባብሳሉ የሚል ጥርጣሬ እየተሰነዘረ ባለበት ወቅት ነዉ። የስልካቸዉ መጠለፍ ያስቆጣቸዉ ሜርክል በሳምንቱ መጀመሪያ ከ70 ሚሊዮን በላይ የስልክና ኢሜል ልዉዉጦች መጠለፋቸዉ ካናደዳት ፈረንሳይ መሪ ፍራንስዋ ኦሎንድ ጋ በጉዳዩ ላይ ዛሬ እንደሚነጋገሩ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ከብራስልስ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ብራስልስ ላይ የተሰባሰቡት የአዉሮፓ ኅብረት አባል መንግስታት መሪዎች የግለሰብ ዜጎችም ሆነ የመሪዎች የግል ጉዳይ ላይ የሚደረግ ስለላ ተቀባይነት እንደማይኖረዉ አመልክተዋል። የፈረንሳይ የዜና ወኪል የኅብረቱ የፍትህ ኮሚሽነር ቪቫነ ሬዲንግ ቃል አቀባይ ኮሚሽነሯ መረጃን የመከላከል ርምጃ የአንጌላ ሜርክል የእጅ ስልክንም ሆነ የግለሰብ ዜጎችን የኢሜል ልዉዉጥ ላይ በእኩልነት ተግባራዊ ልሆን ማለታቸዉን ዘግቧል። ኮሚሽነሯ የኅብረቱ ጉባኤ ማብራሪያ የሚጠይቅበር ሳይሆን ርምጃ የሚወስድበት ጊዜ አሁን ነዉ ማለታቸዉም ተጠቅሷል። ከወራት በፊት ለአዉሮፓ የመረጃ መከላከል ህግ እንዲጸድቅ ቀርቦ 28 አባል መንግስታት በጉዳዩ ልዩነት ስለነበራቸዉ ታግዷል። የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽነር ሆሴ ማኑዌል ባሮሶም በበኩላቸዉ አዉሮጳዉያን የግለሰብን የግል ጉዳይ ማክበርን እንደመሠረታዊ መብት ይመለከቱታል ነዉ ያሉት። የኅብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ዛሬ እና ነገ የኤኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ጉባኤ ለማካሄድ የተሰባሰቡ ሲሆን የጀርመን መራሂተ መንግስት ስልክን የመጠለፍ ወሬ ትኩረታቸዉን ወደሌላ ሳይስብ እንዳልቀረ እየተነገረ ነዉ።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሂሩት መለሰ
 Source: www.dw.de

በዓለም ላይ ሰላሳ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በዘመናዊ ባርነት እንደሚማቅቁ ባርነትን ለማጥፋት የሚታገል አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ባለፈው ሳምንት አስታውቆል። 
« ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽን» የተባለው ይኼው አዲስ ተቋም በርካታ መረጃዎችን አሰባስቧል። አላማው ዘመናዊውን ባርነት በተቻለ ፍጥነት ማስቀረት ነው።
ሊዊዘ የ 14 ዓመት ልጅ ነበረች ቀጣሪዋ የወሲብ ጥቃት ሲያሰርስባት እና ሲደበድባት። ይህም አልበቃ ብሎ አፍሪቃ የሚኖሩት ዘመዶቿ እንደተገደሉ ትሰማለች። ቀጣሪዋም ገዳዮቹን የላከው እሱ እንደሆነ ይነግራታል። ወጣቷ ከአንድ አመት በፊት ከምትኖርበት መንደር ወደ ጀርመን ስትመጣ ቀጣሪዋ ትምህርት ቤት እንደምትሄድ ነበር ቃል የገባላት፣እዚህ ስትመጣ ግን የጠበቃት ሌላ ነው። አማራጭ ያጣችው ወጣት ወደ ሴተኛ አዳሪነት ስራ ትገባለች።« ለሶስት አመት ያህል ደሙ አላቆመልኝም።»

ሊዊዘ በአሁኑ ሰዓት ደቡብ ጀርመን ውስጥ በሚገኝ ለተጎጂዎች በተዘጋጀ ማቆያ ትኖራለች። የበደል ጊዜው አልፎላታል። ይሁንና ሰላሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በዓለም ላይ የዘመናዊ ባርነት ሰለባ እንደሆኑ ነው « ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽን» የተሰኘዉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ድምዳሜ ላይ የደረሰው። በተለይ በአፍሪቃ እና በእስያ ለዘመናዊ ባርነት የሚዳረጉት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነዉ። ሕንድ፥ ቻይና ፣ፓኪስታን እና ናይጄሪያ ቀዳሚውን ቦታ ይዘዋል። ሩስያም ከመጀመሪያዎቹ 10 ሀገሮች ተርታ ተሰልፋለች። ጥናቱ እንደሚያሳየው ከሆነም ማንኛውም አህጉር ይሁን ሀገር ከዘመናዊ ባርነት ነፃ አይደለም።
በሩሲያ የወሲብ ብዝበዛ ይደርሳል፣ በብራዚል በቤት ሰራተኞች ላይ ግፍ ይፈጸማል ። በቻይና የግዳጅ ስራ አለ፣ በህንድ እና ሄይቲም እንዲሁ ሰዎጥ ለባርነት ያዳረጋሉ ። የ« ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽን» አጥኚ ኬቪን ባሌስ ለዶይቸ ቬለ በሰጡት መግለጫ፤
የባርነት ዓይነቶችና እና መፍትሄዎቹ እንደ ሀገሩ ይለያያል ይላሉ ።«አንድ ወጥ መፍትሄ የሚሆን የለም። በየሀገሩ ያለውን ልዩ ሁኔታ መመልከት ያስፈልጋል። »
ስለ ዘመናዊ ባርነት ጥናት ያደረጉት ባገኙት ውጤት መሰረት ጀርመን ውስጥ 10,500 የሚሆኑ ሰዎች ከባርነት ጋር በሚስተካከል ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት ። ኬቪን ባሌስ በእንዲሁ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ትክክለኛ ቁጥሩ ማወቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ ። « የተሸፋፈነ የወንጀል ስራ ነው። ስለሆነም የወንጀሉን ብዛት ለማወቅ ከባድ ነው።»
መዘርዝር ሁሌም አሻሚ ነው። ተቋሙ ያገኛቸውን የተወሰኑ መረጃዎች ወስዶ በመላው ሀገር በዘመናዊ ባርነት ውስጥ የሚገኙት ቁጥር ይህን ያህል ነው ማለት ማነጋገሩ አልቀረም። ባሌስ ለዚህ መልስ አላቸው። « ባርነት እንደ ተላላፊ በሽታ ነው። አመቺው ወይንም ትክክለኛውን ቁጥር እስክናገኝ የምንጠብቅ ከሆነ በመካከል በርካቶች በባርነት ይሰቃዩና ይሞታሉ። ማንም ሊረዳቸው አይችልም።»
« ቴሬ ደ ሆም ዶችላንድ» የተባለው ህፃናትን የሚረዳው የጀርመን ድርጅት ለመላው ዓለም ያሰባሰቡት መረጃ ጥሩ መሆኑን የህፃናት መብት ጉዳዮች ተመራማሪዋ -ባርባራ ኩበርስ ከዶይቸ ቬለ ጋ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል። እንደሳቸው ከሆነ የተቋሙ የባርነትን ትንታኔ የሚወደስ ነው።« አንድን ሰው ግዳጅ ውስጥ የሚጥልን ነገር ሁሉ እንደ ባርነት ነው የሚመለከቱት። ለምሳሌ ያለ እድሜ ጋብቻ። ይህን ደግሞ እኛ በመልካም እናየዋለን።»
የአንዳንድ ሀገሮች አሀዝ መስተካከል ያለበት ቢሆንም በአጠቃላይ ተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጣው ዘገባ ግልፅ ነው ይላሉ ኩበርስ ። ይህ መሆኑ አንዳንድ መንግስታት በጥናቱ ላይ ትክክለኛውን ቁጥር ፍለጋ እንዲያስቡበት ምክንያት ይሆናል ባይ ናቸው ኩበርስ።
« ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽን» እንደ ቢል ጌትስ ባሉ በርካታ ፤ሀብታቸው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ባለሀብቶች እንደሚደገፍ የተቋሙ ቃል አቀባይ ገልፀዋል። የድርጅቱ አጥኚ ኬቪን ባሌስ ዓለም አቀፉ የባርነት መዘርዝር አሁን ባለበት ሁኔታ በየአመቱ ተሻሽሎ መቅረብ አለበት ይላሉ። አላማውም 30 ሚሊዮን ግድም የሚሆን ሰው በዘመናዊ ባርነት እንዳይማቅቅ ለማድረግ ሲሆን ፤ ምባልባትም ቁጥሩን በሚመጡት 30 ዓመታት ወደ በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ተበዳዮች ዝቅ ማድረግ ያቻላል ብለው ያምናሉ።
ክላውስ ያንስ
ልደት አበበ
ሂሩት መለሰ
Source: www.dw.de
 

ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሚዋጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ባለፈው ዓርብ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ ያተኮረ በተለይም አዲስ ኣበባ በሚገኘው እና ማዕከላዊ ተብሎ በሚታወቀው የፌደራሉ የምርመራ ማዕከል በእስረኞች ላይ ይፈጸማሉ ባላቸው ሰብዓዊ ሰቆቃዎች ላይ ያነጣጠረ አዲስ ሪፓርት ይፋ ኣድርገዋል።
ሰብዓዊ መብት ሲባል በነገስታት መልካም ፈቃድ የሚቸሩ ወይንም መንግስታት ከሚመሩባቸው ህግጋተ መንግስታት የሚመነጩ ብቻ ሳይሆኑ በ ተ መ ድ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች መሰረት ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ በተፈጥሮ የተቀዳጁኣቸው መሰረታዊ የሰው ልጅ መብቶች ናቸው። በእነዚህ ህጎች መሰረት ደግሞ እንደ መኖ ኣልባሳት እና መጠለያ የመሳሰሉ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ጨምሮ ዜጎች እንደ ህክምና እና ትምህርት የመሳሰሉ ማህበራዊ ፍላጎቶችን ሁሉ የማግኘት መብት ኣላቸው።
እናም ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት እንዲያውም ዓስርተ ዓመታት ማለት ይቻላል በረኃብ አለንጋ ከሚገረፈው የኢትዮጵያ ህዝብ አንጻር ለምን የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸው እንደ ምክኒያት አዲሶቹ
መንግስታት በቀድሞዎቹ ላይ እያላከኩም ቢሆን መልሳቸው ግን ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ድህነት። በእርግጥ የፖሊሲ ችግሮች ሳይዘነጉ ከድህነት ወለል በታች በምትገኘው ኢትዮጵያ ኣምኖ ለመቀበል ማስቸገሩ ባይቀርም ኣይደለም ብሎ ለመከራከር ግን ሊከብድ ይችላል።
ሌሎች በርካታ የግል እና የቡድን መብቶች በገኃድ ሲጨፈለቁ እና በዚሁ ምክኒያት ሰዎች ሲታሰሩ ሲሰቃዩ እና ሲገደሉ ግን የሂዩማን ራይትስ ዎች የበላይ ኃላፊዎች እንደሚሉት በየኣጋጣሚዊ ከየኣቅጣጫው በተለያየ መልኩ ተቃውሞ እና ውግዘት ተለይቶት ኣያውቅም። ለዚህ ግን ባለስልጣናቱ ኣንድም እንደተለመደው ከጥያቄ መራቅ እና ኣሊያም ከእውነት የራቀ የፈጠራ ወሬ እያሉ ከመካድ ያለፈ ምላሽ የላቸውም የሚለው ሂዩማን ራይትስ ዎች ባሳለፍነው ሳምንት ማገባደጃ ላይም የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታ የሚያብጠለጥል አዲስ ሪፖርት ኣውጥተዋል።
በዚሁ ባለፈው ዓርብ ይፋ በሆነው እና 70 ያህል ገጾች ባሉት የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ መሰረት በኢትዮጵያ እስር ቤቶች በተለይም አዲስ ኣበባ በሚገኘው እና ማዕከላዊ ተብሎ በሚታወቀው የፌደራሉ የምርመራ ማዕከል በሚገኙ እስረኞች ላይ ይፈጸማሉ የተባሉ ሰቆቃዎችን ለማጋለጥ ተሞክረዋል። ከሁሉም በላይ በሪፖርቱ መሰረት የፖለቲካ እስረኞች ግርፋት ወይንም ቶርችን ጨምሮ ፈታኝ በሆነ ኣያያዝ እየተሰቃዩ መረጃ እንዲአጡ ይደረጋሉ። የሐሰት ሰነድም እንዲፈርሙ ይገደዳሉ ተብለዋል። ይኸው መረጃ ኣንዳንዴ እስረኞቹ ተከሰው ችሎት በሚቀርቡበት ሳዓት እንደ ማስረጃ እንዲቀርብባቸው የሚደረግበት ኣጋጣሚም እንዳለ ተወስተዋል።
35 የቀድሞ እስረኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን ዋቢ በማድረግ ሪፖርቱ እንደገለጸው በዚሁ በማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል እስረኞች በጥፊ በእርግጫ በጠመንጃ ሰደፍ በዱላ እና በተለያዩ ነገሮች መደብደባቸውን ለሆዩማን ራይትስ ዎች ኣስረድተዋል። ኣንድ ከኦሮሚያ የተያዘ የኦሮሞ ተማሪም ለወራት እጆቹን በካቴና እና እግሮቹን በእግር ብረት ታስሮ ለምግብም ሆነ ለመጸዳዳት በእስረኞች እርዳታ ብቻ መክረሙን በምሬት ያስታውሳል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘግበዋል።
በሂዩማን ራይትስ ዎች የኣፍሪካ ጉዳዮች ም/ዳይሬክተር የሆኑት ሚ/ስ ሊስሌ ሌፍኮቭ እንደሚሉት ደግሞ የማዕከላዊው እስር ቤት በእሳቸው ኣባባል ማጎሪያ ቤት የተለመዱ ሶስት ክፍለ ማጎሪያዎች ኣሉት። ኣንደኛው ሰዎች ያለ መብራት ተነጥለው ለብቻ የሚታሰሩበት እና ጭለማ ቤት የሚባለው ነው። ሁለተኛው ለግርፋት የተመቻቸው እና በእስረኞቹ ኣጠራር ጣውላ ቤት የሚባለው ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ በኣንጻራዊነትም ቢሆን የተሻለ እና እስረኞች እየተንቀሳቀሱ በጋራ የሚታሰሩበት እና ከዚሁ የተነሳ ሸራተን ተብሎ የሚታወቀው ነው።
ሌላው ኣስቸጋሪ ጉዳይ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው እስረኞች ከዘመዶቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው እንዳይገናኙ መደረጉ ነው። ምክኒያቶቹ ደግሞ ሚ/ስ ሌፍኮቭ እንደሚሉት እስረኞችን ኣስፈራርቶ ኣሰቃይቶ እና ኣደናግሮ መረጃ ለማወጣጣት እና ቢያንስ ጉልህ የሆኑ የግርፋት ኣሻራዎች እንዳይታዩ ለማድረግም ጭምር ነው።
በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ይዞታ ይበልጥ እየተበላሸ የመጣው የተጭበረበረውን የ2005ቱን ምርጫ ተከትሎ ሲሆን ከ2010 ዓ ም ወዲህ በተለይ ህወኃት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያካህደው የመብት ጥሰት ህገ ወጥ ብቻም ሳይሆን ሰብዓዊነትም የጎደለው መሆኑን የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ኣመልክተዋል።
የጸረ ሽብር ህግ የተባለው የኢትዮጵያ ህግም ይላል ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተቃዋሚዎችን ለማፈን ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን ለማሽመድመድ የኃይማኖትም ሆነ የብሔር ተቐማት ኃላፊዎችን ለማሰር እና በኣጠቃላይ ሰብዓዊ መብትን ለመጣስ የሚጠቀሙበት ተጨማሪ መሳሪያ ሆነዋል።
ከኢቲኂጵያ መንግስት በኩል የጠ/ሚ/ሩ ቃል ኣቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ግን የተባለው ሁሉ ከዕውነት የራቀ እና የተለመደ የሂዩማን ራይትስ ዎች ተራ ድራማ ነው ሲሉ ኣጣጥለውታል።
መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሺን ሊቀመንበር ኣንባሳደር ጥሩነህ ዜናም ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በተቀራረበ መልኩ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባን ደካማ ሪፖርት ብለውታል።
የቀድሞው የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ሰመጉ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ሞላ ግን በዚህ ኣይስማሙም። እንደ አቶ እንዳልካቸው እምነት የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ትክክለኛ እና ተጨባጭ ሪፖርት ነው።
በኢትዮጵያ እስር ቤቶች የቶርች ሰለባ ከሆኑት መካከል ደግሞ አቶ ሁሴን ኣህመድ በኢትዮጵያ እስረኖች ላይ ቶርች ስለመካሄዱ ኣንድ እና ሁለት የለውም ይላሉ። በኣሁኑ ጊዜ በኖርዌይ ኣገር የሚኖሩት አቶ ሁሴን ከደረሰባቸው ድብደባ የተነሳ አካላዊ እና አእምሮኣዊ ጉዳት እንደ ደረሰባቸው ይናገራሉ። ከዚሁ የተነሳ ያለ ድጋፍ መንቀሳቀስ እንደማይችሉም ኣስረድተዋል። አቶ ሁሴን ኣህመድ ይህንኑ ለዓለም ህብረተሰብ ለማሳወቅ ከዓለም ዓቀፉ የጸረ ቶርች ኮሚቴ ጋርም እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ጃፈር ዓሊ
ሂሩት መለሰ
Source: www.dw.de

ከዛጒዌ ስመ ጥር ነገሥታት አንዱ በነበሩት በንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ዘመነ መንግሥት ከተሠሩት ኪነ ሕንጻዎች አንዱ የኾነው ይምርሐነ ክርስቶስ፤ የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ የ2014 ተተኳሪ መካነ ቅርስ (2014 World Monuments Watch) ሆኖ ተመረጠ፡፡
ፈንዱ መስከረም 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ዋና ጽ/ቤቱ በሚገኝበት በኒው ዮርክ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው÷ እ.አ.አ በ2014 ዓለም በትኩረት ሊያውቃቸው፣ ሊጠብቃቸውና ለትውልድ ሊያስተላለፍላቸው ይገባል ካላቸው የ41 አገሮች ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ልዩ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚታይበት የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ አንዱ ኾኖ መመረጡ ተገልጧል፡፡
“ወርልድ ሞኑመንትስ ዎች” በተሰኘው ፕሮግራሙ ለአደጋ የተጋለጡና ዝነኛ የቱሪስት መስሕብ የኾኑ ታሪካዊ ኪነ ሕንፃዎችንና

ባህላዊ መካነ ቅርሶችን በማስተዋወቅ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በመለገሥ ዘመን ተሻጋሪ እንዲኾኑ ዓለም አቀፍ ቅስቀሳ የሚያደርገው ወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ፣ በዝርዝሩ ያካተታቸው የተመረጡ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙና በአግባቡ እንዲጠበቁ በዓለም ዙሪያ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ የዓለም ቅርሶች የፈንዱ ተጠቃሚ ሲኾኑ ከእኒህም መካከል ፈንዱ እ.ኤ.አ በ1966 ሲቋቋም የክብካቤና ድጋፍ ሥራውን የጀመረባቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደስ እንደሚገኙበት በመግለጫው ተመልክቷል።
የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ በዓለም አቀፍ ፈንዱ ተመራጭ እንዲኾን በመጠቆምና ለምርጫው የሚያግዙ መረጃዎችን በማቅረብ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ለአዲስ አድማስ የገለጸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ክብካቤና ልማት ማኅበር፤ መካነ ቅርሱ የ2014 የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ ተመራጭ መኾኑ ኪነ ሕንጻውን የበለጠ ለማስተዋወቅና ለማልማት ዕድል ይሰጣል ብሏል፡፡ ቅርሶች ዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ያበረክቱ ዘንድ ራእይ የሰነቀው ሀገር በቀል ማኅበሩን ጨምሮ በቅርስ ክብካቤ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ የሥራ ሓላፊዎችና ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የብዙኀን መገናኛና ሌሎች አካላት ጋራ በመተባበር እንንዲንቀሳቀሱም ምቹ ኹኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡
ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት በሰሜን ወሎ ወግረ ስኂን በሚባል ቦታ ሰፊና ግርማ ሞገስ ባለው የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ በውኃ ላይ እንደታነፀ የሚታመነውና ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይበት ይምርሐ ክርስቶስ÷ በአገራችን ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውን የቤተ መንግሥት ሕንጻ፣ በድንቅ ጥንታዊ ሥዕሎችና ንድፎች ያሸበረቀ ቤተ መቅደስ አሰናኝቶ የያዘ መካነ ቅርስ ነው፡፡ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች፣ ያልፈረሱና ዕድሜ ጠገብ የሰው ዐፅሞች፣ የሀገር በቀል ዕፀዋት ጥቅጥቅ ደንና ማራኪ መልክአ ምድር የሚገኙበት ነው፡፡

Source: http://www.addisadmassnews.com/
 
ዚምባቡዌ ላይ የአደንዛዥ እፅ ዝዉዉርና አጠቃቀምን አስመልክቶ የሚካሄደዉ ጉባኤ፤ መሪዎቹ ወሳኝ ርምጃ ካልወሰዱ የአህጉሩን መረጋጋት ሊጎዳ እንደሚችል አመለከተ። የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብና በተመድ የእፅ ተከታታይ ጽ/ቤት አፍሪቃ ዉስጥ ሕገ ወጥ የአደንዛዥ እፅ ዝዉዉርን ለመግታት የሚያስችል አዲስ ርምጃ ላይ እየመከሩ ነዉ።
የአፍሪቃ ኅብረት የማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ዶክተር ኦላዋሌ ማየጉን እንደሚሉት አፍሪቃ በአህጉር ደረጃ የHIV ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ባደረገችዉ ጥረት ዉጤት እንዳስመዘገበች ሁሉ፤ ቀጣይ ዘመቻዋን ሕገ ወጥ የአደንዛዥ እፅ ዝዉዉርንና አጠቃቀምን መግታት መሆን ይኖርበታል፤
      «የበሽታዉ ስርጭት በአዲስ መልክ ይነሳል የሚል ፍራት ከኖረ ሊሆን የሚችለዉ የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎችን በመርፌ በመዉጋት ነዉ የሚሆነዉ። ከሕገ ወጥ የእጽ ዝዉዉርና ከተደራጀ ወንጀል የሚገኘዉን በርካታ ገንዘብ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ለማደናቀፍና ምርጫዎችን ለማወክ እያዋሉት ነዉ። በድፍረት ዴሞክራሲን ለማደናቀፍና ወደኤኮኖሚያችን ገብቶ የሚፈጥረዉን ዝብርቅርቅ ለማስወገድና ም በተደራጀ
ወንጀል የሚገኝ ገንዘብን አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። በማሊና ጊኒ ባሳዉ የተፈጠረዉን ትርምስ መዉሰድ ይቻላል።»
     ይህን መሰሉን ሕገ ወጥ የአደንዛዥ እፅ ዝዉዉርና አጠቃቀም ለመግታትም አፍሪቃ እና የተመድ በጋራ ጥረት ጀምረዋል። ዶክተር ማይየጉን በኬንያ ዋና ከተማ በቅርቡ በአንድ የገበያ አዳራሽ ዉስጥ የተፈጸመዉ ጥቃት የተደራጀ ወንጀል አፍሪቃን መረጋጋት ስጋት ላይ የሚጥል ታላቅ ፈተና የመሆኑ ማረጋገጫ ነዉ። ናይጀሪያዊዉ ማይየጉን የአፍሪቃ ኅብረት የአደገኛ እፅ ቁጥጥር እና ወንጀል መከላከል የተግባር እቅድ አስፈጻሚ የሆነዉ የኅብረቱ ኮሚሽን አባል ናቸዉ። ዶክተሩ ወንጀለኞች የአፍሪቃ ሃገራትን ክፍት ድንበሮችና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰዉን ድህነት ይጠቀማሉ ባይ ናቸዉ። ወደአዉሮጳና ምዕራብ ሃገራት የሚጓዘዉ አደንዛዥ እፅ መሸጋገሪያም አፍሪቃ መሆኗን ያመለክታሉ።
     «ከደቡብ አሜሪካ የሚመጣዉ ኮኬይን በአብዛኛዉ በምዕራብ አፍሪቃና ጥቂቱ ደግሞ በደቡብ አፍሪቃ በኩል ነዉ የሚያልፈዉ። ከአፍጋኒስታን የሚመጣዉን ሄሮይን ብንወስድ ደግሞ የሚያልፈዉ በምስራቅ አፍሪቃ በኩል ነዉ። አፍሪቃ ዉስጥ ከግጭት ወጥተዉ ያልተጠናከሩ በርካት ሃገራት መሸጋገሪያ እየሆኑ ነዉ። አንዳንድ አደንዛዥ እፆችም እዚያዉ ይቀራሉ። ስለዚህ በአህጉሪቱ የሚታየዉ የአደንዛዥ እፅ አጠቃቀምም በእነዚህ በሚቀሩት ላይ የሚመሠረት ነዉ።»
   
በጉባኤዉ የተገኙት የተመድ የአደንዛዥ እፅ ክትትል ቢሮ ኃላፊ ሻብ ሳላህ ለተሰብሳቢዎቹ ያመለከቱት ጽሕፈት ቤታቸዉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሕገወጥ የአደንዛዥ ዝዉዉርና አጠቃቀምን በመዋጋት ሂደት ያካበተዉን ልምድ አፍሪቃ ዉስጥም ለማዋል እንደሚሻ ነዉ።
«የተመድ የአደንዛዥ እፅ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት፤ አፍሪቃ ለልማት ማለትም በመላ አህጉሪቱ የትምህርት፣ የኤኮኖሚ እድገት እና የጤና ችግሮች ዋነኛ እንቅፋት የሆነባትን ችግር ይገነዘባል። አፍሪቃ ዉስጥ የአደንዛዥ እፅ መጠቀም በተለይም በወጣቶች ዘንድ በፍጥነት እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ነዉ። የተመድ የአደንዛዥ እፅ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት አባል ሃገራት የአደንዛዥ አጠቃቀም፤ ዝዉዉር፣ ሙስናና አሸባሪነትን የመታገል ጥረትና አቅማቸዉን እንዲያጠናክሩ የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል።»
ከመላዉ አፍሪቃ የተለያዩ መንግስታትን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በመወከል በጉባኤዉ የተገኙ ባለሙያዎች፤ ወደአህጉሪቱ የሚዘልቀዉን የአደንዛዥ እፅ አቅርቦት ለመቀነስ የታየዉ ተነሳሽነት ተስፋ እዳሳደረባቸዉ እየገለጹ ነዉ።
ኮሎምበስ ማቩንጋ
ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ
Source: www.dw.de
ዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በዓለማችን ከስምንት መቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እየተራበ የሚታየዉ የምግብ ብክነት ተቀባይነት እንደሌለዉ አመለከተ። ድርጅቱ ዛሬ ይፋ ባደረገዉ ዘገባዉ የምግብ ማጣት ብቻ ሳይሆን የተመጣጠነና በቂ ምግብ አለማግኘት አካላዊ እድገታቸዉ ለእድሜያቸዉ የማይመጥን ልጆች ቁጥርም 165 ሚሊዮን መድረሱንም አስታዉቋል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለፈዉ ዓመት የመኸር ዝናብ መጠንና ስርጭት የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ተስፋ አሳድሯል። የምግብ ርዳታ የሚጠብቀዉም ሶስት ሚሊዮን አይሞላም።
በዓለማችን በአንድ ወገን የተትረፈረፈ ምግብ እየተመረተ ለብክነት ሲዳረግ በሌላዉ በኩል ደግሞ የዕለት ጉርስ የሚሻዉ ወገን በረሃብ አንጀቱ መታጠፉ አግባብነት የለዉም ይላል የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ማለትም FAO። እንድርጅቱ ዘገባ ከሆነም በየዓመቱ በዓለም ከሚመረተዉ የምግብ እህል አንድ ሶስተኛ እጁ ማለትም 1,3 ቢሊዮን ቶን ከተራቡት ጉሮሮ የሚገባ ሳይሆን እንደቆሻሻ የሚጣል ነዉ። በዓለም ወደሁለት ቢሊዮን ሰዎችም ለጤና እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የቪታሚንና የማዕድናት እጥረት ተጎጂም እንደሆኑ FAO ዘገባዉ ያመለከተዉ።
ለምግብ ብክነቱ የዝናብ እጥረትና ድርቅ ሁኔታ በሚያስከትለዉ ተጽዕኖ የሚበላዉ መጥፋት ብቻ ሳይሆን እንደየአካባቢዉ የአመጋገብ ልማድም ለምግብነት የማይዉሉ መኖራቸዉ ችግሩን ማባባሱ ነዉ የተገለጸዉ። FAO እንደሚለዉ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ዉስጥ የፍየል ርባታ ላይ ያተኮረዉ ፕሮጀክት የወተት ፍጆታንና በእሱም የሚገኘዉን ገቢ በብዛት ጥቅም ላይ ማዋል አስችሏል።
ያም ሆኖ ግን እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ዓለም ዓቀፍ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸዉን ድርጅቱ አስታዉቋል። የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ አቶ ምትኩ ካሣ የምግብ ለሥራ አገልግሎት በመኖሩና የተረጂም ቁጥር በመቀነሱ ሀገሪቱ ዘንድሮ ብዙም የምግብ እርዳታ የምትጠብቅበት ደረጃ ላይ እንዳልሆነች ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም በአርብቶ አደሩ አካባቢ ችግሩ መኖሩን አመልክተዋል።
ርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ወገኖች በተገቢዉ ጊዜና መጠን የምግብ ድጋፍ እንደሚያገኝ ያመለከቱት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ረድኤቱ ከሀገር ዉስጥም ከዉጭም እንደሚገኝም ገልጸዋል። በአርብቶ አደሩ አካባቢ የዝናብ እጥረት እና ከአኗኗር ይትበሃል አኳያ የምግብ ርዳታዉ መኖሩን ቢገልጹም ርዳታዉ ጊዜያዊ መፍትሄ እንጂ ዘላቂ ለዉጥ አያመጣምና ያንን ለመለወጥ የተጀመሩ እቅዶች ተግባራዊ እየሆኑ መሆናቸዉንም አቶ ምትኩ ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በዝናብ አጠር አካባቢዎች እንዲሁም በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት ለችግር ተጋልጠዉ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ወገኖች መኖራቸዉን የክልሉ ግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት አቶ አበራ ለማ አርሶ አደሮቹ ከዚህ ሁኔታ የሚወጡበት አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ ነዉ ይላሉ። እርዳታዉም ሥራ ሠርተዉ በምግብ መልክ፤ አለያም በገንዘብ ብድር የሚሰጣቸዉ መሆናቸዉንም ዘርዝረዋል። የዘንድሮዉ የዝናብ ሁኔታ ጥሩ እንደነበር በማመልከትም የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ ነዉ ሁለቱም የሚያመለክቱት።
ሸዋዬ ለገሠ
አርያም ተክሌ
Source: www.dw.de
 
በዘር ማጥፋት፥በሰብአዊ ፍጡር ላይ በተፈፀመ ወንጀል እና በጦር ወንጀል የሚጠረጠሩ ፖለቲከኞችን እንዲመረርምር፥ በተረጋገጠባቸዉ ላይ እንዲፈርድ የተቋቋመዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ግን እስካሁን ክስ የመሠረተዉ በስምት የወንጀል ጭብጦች ነዉ።በስምንቱም ጉዳዮች የከሰሳቸዉ፥ ወይም የፈረደባቸዉ ፖለቲከኞች በሙሉ ግን አፍሪቃዉያን ናቸዉ።
በ1919 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያን አቆጣጠር ነዉ) የጦር ወንጀለኞችን የሚቀጣ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ሐሳቡ ሲነሳ፣ ሲወድቅ፣ በ1948 ዳግም ሲነሳ፣ ደንቡ ሲረቀቅ፣ ረቂቁ ሲወድቅም አብዛኞቹ አፍሪቃዉያን ከአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች ነፃ ለመዉጣት ገና እየገደሉ ይሞቱ ነበር።1975 በደራዉ ክርክር ዉስጥም አፍሪቃዉያን አልነበሩበትም።በ1998 የመመሥረቻ ዉሉን ለመፈረም፣ በ2002 ለማፅደቅ ግን አፍሪቃ ይንጋጋ ገባ።ለፍርድ ቤቱ በርካታ አባላትን በማሰለፍ አፍሪቃ አንደኛ ናት።ፍርድ ቤቱ ከአፍሪቃዊ ዉጪ በአንድም የሌላ አሐጉር ወንጀለኛ ላይ
አልበየነም።አንድም የሌላ አሐጉር ተጠርጣሪ አልተከሰሰም። ከአፍሪቃዉያን ሌላ አንድም ሐገር ፍርድ ቤቱን አልተቃወመም። ድንቅ መስተጋብር።እንበል ይሆን?

የአፍሪቃ መሪዎች የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (ICC) አባል ለመሆን ሲሽቀዳደሙ ከዚያ በፊትና በሕዋላም-ዩጋንዳ አንድ መሪ ነበሯት።አሏትምም።ፕሬዝዳት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ።ፍርድ ቤቱ የሱዳኑ ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አልበሽር በተገኙበት እንዲያዙ የእስራት ዋራንት ሲቆርጥባቸዉም ሙሴቬኒ በነበሩ-ባሉበትም ሥልጣን ላይ ነበሩ።ምናልባት የረጅም ጊዜ ተቀናቃኛቸዉ በመዋረድ፥ መከሰሳቸዉ ተደስተዉ ይሆን-ይሆናል።በይፋ ያሉት ግን አልነበረም።

የሙሴቪንን መንግሥት በሐይል አስወግዶ ዩጋንዳን በመፅፍ ቅዱሱ አስርቱ ትዕዛዛት መሠረት ለመግዛት የሚፋለመዉ የሐሪቱ አማፂ ቡድን መሪዎች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲዳኙ የጠየቁትም ራሳቸዉ ሙሴቬኒ ነበሩ።የኬንያ ፖለቲከኞች በምርጫ ዉጤት ሰበብ ጎሳን ከጎሳ አጋጭተዋል፥ ሰዉ አስገድለዋል በሚል ጥርጣሬ ሲከሰሱም የዩጋንዳ መሪ በይፋ ያሉት አልነበረም።


ተከሳሾቹ የኬንያን የፕሬዝዳትነትና የምክትል ፕሬዝዳትነት ሥልጣን ከያዙ በኋላ ግን አንጋፋዉ ፕሬዝዳንት የደገፉትን፥ ሐገራቸዉን አባል ያደረጉበትን፥ ተቃዋሚዎቻቸዉ እንዲከሰሱ የጠየቁትን፥ ፍርድ ቤት ይተቹ፥ በዘረኝነት ይወቅሱ ገቡ።

«(የኬንያዉ ግጭት) ሕጋዊ ጉዳይ አይደለም።ርዕዮተ-ዓለማዊ ነዉ።መያዝ ያለበትም በዚሕ መሠረት ነዉ።እነዚሕ የICC ሰዎች ግልብ ናቸዉ።»ሌላ ጊዜም ቀጠሉ።ጠንከር፥ ከረርም አሉ።«እኒያ ሥለ ጎሳ እና ሐራጥቃ የሚያወሩ የአፍሪቃ ጠላቶች ናቸዉ።በግል ደግሞ የኔ፥ የእናንተም ጠላቶች ናቸዉ።»

የተከበሩት የዩጋንዳ መሪ አይነቱ አቋም በጎቲንገን-ጀርመን ዩኒቨርስቲ የወንጀለኝ ጉዳይ የሕግ-ባለሙያ ካይ አምቦስ እርስ በርሱ የሚቃረን ይሉታል።«ICC የዩጋንዳ አማፂያንን እንዲከስ ጉዳዩን ለፍርድ ቤቱ የመሩት የዩጋንዳዉ ፕሬዝዳት ራሳቸዉ ናቸዉ።እና አሁን የሚሰነዘረዉ ትችት በጣም (ከድርጊቱ) የሚቃረን ነዉ።አሁን የአፍሪቃ ሕብረት ዉስጥ የሚደረገዉ ICC የመቃወም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነዉ።በተለይ በግልፅ የሚታየዉ ጉዳዩ ከነካቸዉ (ከተከሠሱት) መንግሥታት።»


በሴራሊዮኑ የርስ በርስ ጦርነት የተደረሰዉን ግፍ የሚመረምረዉ የሴራሊዮን ጉዳይ ፍርድ ቤት የቀድሞዉን የላይቤሪያ ፕሬዝዳት ቻርልስ ቴለርን የከሰሰ፥ ያሰረዉም፥ የቀድሞዉ የየኮትዲቯር ፕሬዝዳት ሎራ ባግቦም ከሥልጣን የተወገዱ፥ የተከሰሱ የታሰሩትም በአፍሪቃዉያን መሪዎች ትብብር ነበር።በዚሕም ሰበብ ያኔ ፍርድ ቤቱን የወቀሰ፥ የተቸም አልነበረም።

የሱዳኑ ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አልበሽር ዳርፉር ዉስጥ ተፈፅሟል በተባለዉ ወንጀል ጥርጣሬ ሲከሰሱ፥ በተገኙበት እንዲያዙ ፍርድ ቤቱ ሲያዝ ግን አንዳድ የአፍሪቃ መሪዎች ማንገራገር ጀመሩ።አፍሪቃ ዉስጥ በሥልጣን ላይ ያለዉን መንግሥት በጠመንጃ ዉጊያ አለያም በፖለቲካዊ አመፅ፥ ወይም በምርጫ ለማስወገድ የተደራጀ ሐይል የሌለበት ሐገር ጥቂት ነዉ።

አል-በሽር የዳርፉር አማፂዎችን ለመቅጣት በወሰዱት እርምጃ ከተከሰሱ ጠላት ወይም ተቃዋሚዎቹን ለማጥፋት የሚታገለዉ አፍሪቃዊ መሪ ነግ በኔ ማለቱ አይቀርም።የነቻርልስ ቴለርን ጉዳይ ችላ ያሉት ብዙዎቹ የአፍሪቃ መሪዎች ክሱ አልበሽር ላይ ሲደርስ የማንገራገራቸዉ ትክክለኛ ምክንያት ነግ በኔ የማለት ሥጋት ሊሆን ይችላል።በይፋ የተሰጠዉ ሰበብ ግን ISS በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ዶክተር ሰለሞን ደርሶ እንደሚሉት የዳርፉርን የሠላም ሒደት ያደናቅፈዋል የሚል ነበር።

የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች ብሪታንያ፥ ፈረንሳይና ዩናይትድ ስቴትስ ሌሎች ሠላሳ ሁለት ወዳጆቻቸዉን አስከትለዉ ዓለም የጦር ወንጀለኞች የሚዳኙበት የጋራ ፍርድ ቤት እንዲኖራት በ1919 ሲመክሩ አብዛኞቹ አፍሪቃዉን በአዉሮጳዉያን ቅኝ ገዢዎች ይረገጡ ነበር።ፍርድ ቤት ይቋቋም የሚለዉን ሐሳብ ቀድመዉ ያነሱት የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ነበሩ።የፍርድ ቤቱ ማቋቋሚያ ጥናት ሲቀርብ ግን አሜሪካኖች ተቃዋሚ ሆኑ።ሐሳቡም፥ በሐሳብ ቀረ።

ሐሳቡ በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ዳግም ተነስቶ የፍርድ ቤቱ ማቋቋሚያ ደንብ እስከ መረቀቅ ደርሶ ነበር።ረቂቁ በሁለተኛ ዓመቱ ሲጠናቀቅ ግን ዓለም በቀዝቃዛዉ ጦርነት በምትናጥበት በዚሕ ወቅት የጋራ ፍርድ ቤት ማቋቋም አይቻልም ተብሎ ቀረ።
 
በ1975 እንደገና ሐሳቡ ተነሳ፥ እንደገና ተዳፈነ።የኮሚንስቱ ጎራ ከተፈረካከሰ በሕዋላ ግን ፍርድ ቤቱን የማቋቋሚያዉ ዉል በ1998 ተፈረመ።በሁለት ሺሕ ሁለት ፍርድ ቤቱ ተቋቋመ።የፍርድ ቤቱን መቋቋም የተቃወሙት ሰባት ሐገራት ብቻ ነበሩ።ቻይና፥ ኢራቅ፥ እስራኤል፥ ሊቢያ፥ ቀጠር፥ ዩናይትድ ስቴትስ እና የመን።ሐሳቡን ስታነሳ-ስትጥል፥ ሥታስረቀቅ-ስታግድ የነበረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ የፍርድ ቤቱን መቋቋም ስትቃወም አብዛኞቹ አፍሪቃዉያን ግን መስራቾች ሆኑ።

የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሑዩማን ራይትስ ወች ባልደረባ ኤልዛቤት ኤቬንሰን እንደሚሉት አፍሪቃዉያን ከፍርድ ቤቱ አባል ሐገራት መካከል ከፍተኛዉን ቁጥር የያዙ ናቸዉ።

«የአፍሪቃ ሐገራት ከመሥራቾቹ ሐገራት መሐል ናቸዉ።እነሱ (ICC) ለመቋቋሙ መንገድ ጠርገዋል።ከፍተኛ ቡድንም ናቸዉ።»

እርግጥ ነዉ፥ የዩጎዝላቪያ፥ የሩዋንዳ፥ የሴራሊዮን ወዘተ እየተባሉ የተቋቋሙት ፍርድ ቤቶች በየሐገራቱ የተፈፀሙ ወንጀሎችን መርምረዉ ብይን ሰጥተዋል።ይሰጣሉም።በዘር ማጥፋት፥በሰብአዊ ፍጡር ላይ በተፈፀመ ወንጀል እና በጦር ወንጀል የሚጠረጠሩ ፖለቲከኞችን እንዲመረርምር፥ በተረጋገጠባቸዉ ላይ እንዲፈርድ የተቋቋመዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ግን እስካሁን ክስ የመሠረተዉ በስምት የወንጀል ጭብጦች ነዉ።

የከሰሳቸዉ፥ ወይም የፈረደባቸዉ ፖለቲከኞች በሙሉ ግን አፍሪቃዉያን ናቸዉ።ክስና ብይኑ በተለይ የኬንያ ፕሬዝዳት ኡሁሩ ኬንያታንና ምክትላቸዉን ዊሊያም ሩቶን መንካቱ ያስቆጣቸዉ የአፍሪቃ መሪዎች ፍርድ ቤቱን በዘረኝነት ለመወቅስ ሰበብ-ምክንያታቸዉም ይኸዉ ነዉ።የአፍሪቃ ሕብረትን ተዘዋዋሪ የሊቀመንበርነት ሥልጣን የያዘችዉ የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቴዎድሮስ አድሐኖም ፍርድ ቤቱን የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል እስከማለት ደርሰዋልም።


የኬንያ ምክር ቤት ሐገሪቱ ከፍርድ ቤቱ አባልነቷ እንድትወጣ በቅርቡ ወስኗል።ሌሎቹ የፍርድ ቤቱ አባላት የሆኑት ሠላሳ ሰወስቱ የአፍሪቃ ሐገራትም የኬንያን ፈለግ ይከተላሉ የሚል ሥጋት ነበር። አፍሪቃ ከፍርድ ቤቱ ጋር ሥለሚኖራት ግንኘት ለመነጋገር ባለፈዉ ቅዳሜ ተሰይሞ የነበረዉ የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ግን አባል ሐገራት ከፍርድ ቤቱ አባልነት እንዲወጡ አልወሰነም።
ይሁንና ጉባኤዉ በስልጣን ላይ ያሉ አፍሪቃዉያን መሪዎች እንዳይከሰሱ ጠይቋል።ጥያቄዉን ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ባንድ ወይም በሌላ መልኩ በበላይነት ለሚመራዉ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የሚያቀርቡ መልዕክተኞችም ወደ ኒዮርክ እንዲሔዱ ጉባኤዉ ወስነዋል።ዶክተር ሰለሞን ደርሶ እንደሚሉት የአፍሪቃ መሪዎች የቅዳሜ ዉሳኔ በጎም-መጥፎም ነዉ።

«ከፍርድ ቤቱ አባልነት በጅምላ መዉጣት የለም።ይሕ ቀና ነገር ነዉ።ይሁንና ከቀረበዉ ጥያቄ አኳያ ማለት በሥልጣን ላይ ያሉ መሪዎች እንዳይከሰሱ መጠየቁ ሲታይ፥ የአፍሪቃ ሕብረት ወይም አባላቱ ከICC ጋር የፈጠሩትን የልዩነት ክፍተት ለመድፈን በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል።»

የሕግ ባለሙያ ሐርሜን ፋን ዴር ቪልት እንደሚሉት ደግሞ በወንጀል የሚጠረጠርን ሰዉ ሥልጣን እሰከሚለቅ መከሰስ የለበትም ማለት ተገቢ አይደለም።ሥልጣን የወንጀለኞች ወይም የተጠርታሪዎች መሸሸጊያ መሆን የለበትምና።

«ሥልጣን ላይ እስካለሕ ድረስ ሥልጣንሕ በወንጀል ከመከሰስ መከታ ሊሆን አይገባም።እንደሚመስለኝ የአፍሪቃ ሕብረት ዓላማ ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ከተገቢዉ ተልዕኮዉ ማሳት ነዉ።»

አሳተም-አላሳተ የአፍሪቃ መሪዎች ጉዳዩን ሥራዬ ብለዉ መያዛቸዉ እርግጥ ነዉ።መሪዎቹ ለቅዳሜዉ ጉባኤና ዉሳኔ የደረሱትም ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በተለይ በኬንያ መሪዎች ላይ የመሠረተዉን ክስና የሚያደርገዉን ምርመራ ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፍ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነዉ።
አሁን ማስጠንቀቂያ አዘል ጥያቄያቸዉን የሚያቀርቡት ለፍርድ ቤቱ አይደለም።ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ነዉ።በምክር ቤቱ ዉስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ካላቸዉ ከአምስቱ ሐያላን በጣም ሐይለኞቹ፥ ቻይና፥ ሩሲያና ዩናይትድ ስቴትስ የፍርድ ቤቱ አባላት አይደሉም።
ይሁንና የአፍሪቃዉያኑ ጥያቄ ለድምፅ ከቀረበ ሐርሜን ፋን ዴር ቪልት እንደሚሉት ጥያቄዉን ዉድቅ ለማድረግ ፍርድ ቤቱን ከሚደግፉት ከፈረንሳይና ከብሪታንያ ያንዳቸዉ ተቃዉሞ በቂ ነዉ።
«ብሪታንያና ፈረንሳይ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ደጋፊዎች ናቸዉ።ዉሳኔዉን ሊሽሩት ይችላሉ።»

የአፍሪቃ መሪዎች አምባገነን ሊሆኑ ይችላሉ።ያሁን ጥያቄያቸዉ ከቀድሞ አቋማቸዉ መቃራኑም አያነጋግርም።ጥያቄቸዉን ለመስማት ወይም ላለስማት፥ ለመቀበልም-ሆነ ላለመቀበል በፍትሑም፥ በዓለም ማሕበሩም መድረክ ዛሬም ወሳኞቹ አፍሪቃን ለዘመናት በቅኝ ገዢነት ሲረግጡ የነበሩት የለንደን እና የፓርስ መንግሥታት መሆናቸዉ በርግጥ ያስተዛዝባል።ግን ለዛሬ ይብቃን።ከዛሬ ጀምሮ ሥለ ዝግጅታችን ያላችሁን አስተያት፥ እንጠብቃለን።ማሕደረ ዜና ቢያስተናገደዉ ጥሩ ነዉ ብላችሁ የምታስቡትን ጉዳይም ጠቁሙን።የሥልክ፥ የደብዳቤና የኤስ ኤም ኤስ አድራሽችን የተለመደዉ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ
 Source: http://www.dw.de



በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መስሪያ ቤት ስራ ከጀመሩ ሁለት ወራት ያስቆጠሩት ምክትል ሚንስትሯ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግሥታቸው በአፍሪቃ በተለይም በቀፍሪቃ ቀንድን የሚከተለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አብራርተዋል። 
በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መስሪያ ቤት ስራ ከጀመሩ ሁለት ወራት ያስቆጠሩት ምክትል ሚንስትሯ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግሥታቸው በአፍሪቃ በተለይም በቀፍሪቃ ቀንድን የሚከተለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አብራርተዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር የአፍሪቃ ጉዳዮች ምክትል ሚንስትር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ መንግስታቸው በአፍሪቃ ቀንድ የሚከተለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተመለከተ ትናንት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
የዋሺንግተን ዲሲው ወኪላችን አበበ ፈለቀ መግለጫውን ተከታትሏል። አበበን ስቱዲዮ ከመግባቴ ቀደም ብሎ በስልክ አነጋግሬዋለሁ። አበበ ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድን በተመለከተ የምትከተለውን ፖሊሲ አስመልክቶ ምክትል ሚንስትሯ የገለጿቸውን አበይት ነጥቦች በማስቀመጥ ይጀምራል።

አበበ ፈለቀ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሂሩት መለሰ
Source: www.dw.de
ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰራተኞች ክፍያቸውን አያገኙም
800 ሺህ ሰራተኞች ያለ ምንም ካሳ ከስራ ይሰናበታሉ
የአገልግሎት፣ የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ክፉኛ ይጎዳሉ
የሩብ አመቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በ0.3 በመቶ ሊቀንስ ይችላል

              ባለፈው ማክሰኞ ማለዳ በይፋ የተዘጋው የአሜሪካ መንግስት፣ መቼ እንደሚከፈት እርግጡን መናገር እንደማይቻልና የአገሪቱ ኮንግረስ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ማካሄጃ ገንዘብ የሚገኝበትን መላ ፈልጎ እስኪያገኝና የጋራ መግባባት ላይ እስኪደርስ ድረስ፣ መንግስት እንደተዘጋ መቆየቱ ግድ እንደሚሆን የዋሽንግተን ፖስቱ ዘጋቢ ብራድ ፕላመር ይናገራል፡፡
የአገሪቱ መንግስት መዘጋቱ በይፋ ከተገለጸበት ቅጽበት አንስቶ ጉዳዩ አለምአቀፍ መነጋገሪያ ሆኗል። የመንግስት መዘጋት በዜጎችና በአጠቃላዩ የአገሪቱ እንቅስቃሴ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ያሳድር
ይሆን የሚለው ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡
የአሜሪካ መንግስት መዘጋቱን ተከትሎ በቀዳሚነት የተደመጠው ተያያዥ ዜና፣ ፓንዳ ካም የተሰኘው የአገሪቱ ብሄራዊ መካነ እንስሳት መዘጋቱ ነበር፡፡ ይሄን የሰሙም ታዲያ፣ ነገሩ የእንስሳቱን ኑሮ ከማመሳቀል አልፎ፣ ይሄን ያህል የከፋና ዜጎችን የሚጎዳ መስሎ አልታያቸውም ነበር፡፡ የዋሽንግተን ፖስት ዘጋቢው ብራድ ፕላመር ግን ጉዳዩ ከዚህም የባሰ የከፋ ተጽዕኖ ያሳድራል ባይ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው የተዘጋው መንግስት ፈጥኖ ካልተከፈተ ገና ብዙ ቀውስ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ብራድ ፕላመር ነገርየው የሚያሳድራቸውን ከፉ ተጽዕኖዎች በዝርዝር ዳሷቸዋል፡፡
ጉዳዩ በአፋጣኝ የሚያሳድረው ትልቁ ተጽዕኖ፣ የአገሪቱን ሰራተኞች ሰለባ እንደሚያደርግ ነው ዘጋቢው የሚናገረው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የአገሪቱ ኮንግረስ አፋጣኝ መፍትሄ ካልፈለገና መንግስት እንደተዘጋ የሚቆይ ከሆነ፣ ከ 2 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ የፌዴራል ሰራተኞች የሚገባቸውን ክፍያ በወቅቱ አያገኙም፡፡ 800 ሺህ ያህሉ ደግሞ ምናልባትም የሰሩበት ገንዘብ ሳይከፈላቸው ያለምንም ካሳ ባዶ እጃቸውን ወደቤታቸው ሊሸኙ ይችላሉ፡፡
የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ማርክ ዛንዲ እንደሚሉት፣ በርካታ ሰራተኞች ከስራ መሰናበታቸው በአገሪቱ የመጨረሻ ሩብ አመት አጠቃላይ የምርት እድገት ላይ 0.3 በመቶ ቅናሽ ይፈጥራል፡፡ ከአገሪቱ ሰራተኞች አብዛኞች የሚገኙባት ሜሪላንድም፣ በየቀኑ በገቢና በሽያጭ ታክስ መልኩ ትሰበስብ የነበረውን 5 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ታጣለች፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ተቋራጮችም እንቅስቃሴያቸው መገታቱን ተከትሎ ሰራተኞቻቸውን በገፍ ይቀንሳሉ፡፡ ይህም ተጨማሪ ቀውስ መፍጠሩ አይቀሬ ነው ተብሏል፡፡
የአገሪቱ የነባር ሰራተኞች ጉዳይ ባለስልጣናት፣ ነገሩ ክፉኛ አሳስቧቸው ለኮንግረሱ ስጋታቸውን እንደገለጹ ተነግሯል፡፡ ባለስልጣናቱ መንግስት ከሁለት ሳምንታት በላይ እንደተዘጋ የሚቆይ ከሆነ፣ ለአካል ጉዳተኞች ወይም ለጡረተኞች የሚሰጡት ቤሳቤስቲን ሳንቲም እንደማይኖራቸው አስጠንቅቀዋል፡፡ ይህ ደግሞ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ 3 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የቀድሞ ሰራተኞችን ተጠቂ ያደርጋል፡፡
ባለስልጣናቱ ከኮንግረሱ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ አብዛኞቹ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ህይወታቸውን የሚመሩት ከመንግስት በሚያገኙት ድጎማ በመሆኑና ቀድመው እንዲዘጋጁ መረጃ ስላልተሰጣቸው ጉዳታቸው የከፋ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡
የአገሪቱ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ዲፓርትመንትም ጉዳዩ መላ እንዲበጅለት አበክሮ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ ዲፓርትመንቱ እንደሚለው፣ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል የተባለው ድርጅት አመታዊውን የወቅታዊ ኢንፍሉዌንዛ ፕሮግራም ስራውን ለመስራት ሲዘጋጅ በተከሰተው የመንግስት መዘጋት ሳቢያ ስራውን ለማከናወን ተቸግሯል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ድርጅቱ ለተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር በሚል ለመንግስትና አጋር አካላት የሚያደርገውን ድጋፍ ለማቆም እንደሚገደድ አሳውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በወረርሽኝ ፍተሻ፣ ቤተ-ሙከራ ድጋፍና በሃያ አራት ሰዓት የድንገተኛ ህመም ህክምና አገልግሎት ዘርፎች ይሰጥ የነበረውን አገልግሎትም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ገልጧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት መዘጋት ከሚያሳድራቸው የከፉ ተጽዕኖዎች መካከል የሚመደበው ሌላው ነገር ደግሞ፣ የአገሪቱ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር አብዛኛዎቹን የምግብ ዋስትና ስራዎች ሊያቋርጥ መገደዱ ነው፡፡ ስራቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ ተብለው የተጠቀሱት ሌሎች ተቆጣጣሪ አካላትም አሉ፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ የአየር ብክለትና የጸረ ተባይ መድሃኒቶች አጠቃቀም ቁጥጥሩን፣ የስራ ዲፓርትመንትም የክፍያና የስራ ሰዓታት ወይም የሰራተኞች ደህንነት ህጎችን በአግባቡ ተግባራዊ የማድረግ ስራውን ማቋረጣቸው አይቀሬ ነው እየተባለ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች መሰል ተቆጣጣሪ አካላት ስራ በፈቱበት ሁኔታ፣ የአገሪቱ እንቅስቃሴ ጤናማ ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልም ይላል- የዋሽንግተን ፖስቱ ዘጋቢ፡፡
የአገሪቱ የግብርና ዲፓርትመንትም መንግስት ተዘግቶ በሚቆይባቸው ጊዜያት ሴቶች፣ ጨቅላዎችና ህጻናት ጤናማ ምግብ እንዲያገኙ የሚያደርገውን የገንዘብ፣ የመረጃና የጤና ክብካቤ አገልግሎት ድጋፍ ፕሮግራሙን ሙሉ ለሙሉ ያቋርጣል፡፡ በአገሪቱ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 9 ሚሊዮን እንደሚደርስም ዘገባው ያሳያል፡፡ ከፌደራል ድጋፍ የሚደረግላቸው ፕሮግራሞችም ቢሆኑ ከአንድ ሳምንት የዘለለ እድሜ ሊቆዩ እንደማይችሉ ተነግሯል፡፡
ለአነስተኛ የንግድ ተቋማት የሚደረገው የፋይናንስ ድጋፍና አቅርቦት ሌላው የችግሩ ሰለባ እንደሚሆን የተቀሰው ዘገባው፣ የሚመለከተው የመንግስት አካል ባለፉት አራት አመታት ከ 193 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አነስተኛ የንግድ ተቋማት 106 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ በብድር መልክ መስጠቱን ያስታውሳል፡፡ የሰሞኑ ክስተት ግን ይሄን የገንዘብ አቅርቦት ፈተና ላይ ይጥለዋል እየተባለ ነው፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተሰራ ጥናት፣ አመታዊ ገቢያቸው ከ5 ሚሊዮን ዶላር በታች ከሆነ መሰል የአገሪቱ ተቋማት 41 በመቶ የሚሆኑት ሁኔታው ከሶስት ወራት በላይ የሚቀጥል ከሆነ ሰራተኞቻቸውን ለመቀነስ እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ከአሜሪካ መንግስት መዘጋት ጋር ተያይዞ ተጎጂ ከሚሆኑ ዘርፎች መካከል እንደሆነ በዘገባው የተጠቀሰው የአገሪቱ የቱሪስት ንግድ ዘርፍ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአገሪቱ ብሄራዊ ፓርኮች አገልግሎት ታዋቂዎቹን ዮስማይት፣ ግራንድ ካንዮን፣ አልካትራዝና የኒዮርኩን የነጻነት ሃውልት ጨምሮ ከ400 በላይ ብሄራዊ ፓርኮችን፣ ሙዚየሞችንና የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመዝጋት እንደተገደደ ተነግሯል፡፡ ቱሪስቶችም ወደመጡበት እንዲመለሱ ይደረጋል ተብሏል፡፡ በቱሪዝሙ ዘርፍ የሚፈጠረው ቀውስ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያደርስ የገለጸው ዘገባው፣ እ.ኤ.አ በ1995 በተከሰተው ተመሳሳይ የአገሪቱ መንግስት መዘጋት 7 ሚሊዮን ያህል ጎብኝዎች ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጉን ያስታውሳል፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ኮንግረስ ምርምር አገልግሎት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ክስተቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውና አየርመንገዶች በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያሳጣቸዋል፡፡
በዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ላይ እንደተጠቀሰው፣ በአገሪቱ አነስተኛ ገቢ ላላቸው 1 ሚሊዮን ያህል ህጻናትና ቤተሰቦቻቸው የትምህርት፣ የጤና፣ የምግብና የሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጡ 1ሺህ ስድስት መቶ ያህል ፕሮግራሞች አሉ፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞችም ታዲያ የመንግስትን መዘጋት ተከትሎ ቀስበቀስ ራሳቸውን መዝጋታቸው አይቀሬ ነው ተብሏል፡፡ ለነገሩ አሁንም ተጀምሯል፡፡ በኒዮርክ ካውንቲ መሰል አገልግሎት የሚያገኙ 864 ያህል የቅድመ አጸደ ህጻናት ተማሪዎች ትናንት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል፡፡
ከመንግስት መዘጋት ጋር ተያይዞ ስጋት ውስጥ ከወደቁ ነገሮች መካከል ሌላው ደግሞ፣ የማህበራዊ ደህንነት አገልግሎት ነው፡፡ የአገሪቱ የማህበራዊ ደህንነት አስተዳደር ከአካል ጉዳተኞች የሚቀርቡ የድጋፍና ጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን ተቀብሎ በአግባቡ የሚያስተናግድ በቂ ሰራተኛ ሊኖረው አይችልም ተብሏል፡፡ የቀድሞ ሰራተኞች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች ተቀብሎ የሚያስተናግደው ቦርድ የሚዘጋ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ ይህም ከአካል ጉዳተኝነት ድጋፍና ጥቅማጥቅሞች ጋር በተያያዘ አቤቱታ ያቀረቡ የቀድሞ ሰራተኞች ውሳኔ ለማግኘት፣ የመንግስት ወቅታዊ ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ እንዲጠብቁ ግድ ይላቸዋል፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ የጤና ኢንስቲቲዩትም ነገሩ መላ ይባል እያለ ነው፡፡ የተዘጋው ነገር አንዳች መፍትሄ ካላገኘ፣ የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ ተቋሙ በይፋ ተናግሯል፡፡ መንግስት በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ በህክምና ምርምር ማዕከሉ አገልግሎት ሲሰጣቸው የነበሩ ታካሚዎችን ሳያጋግሙ ከአልጋ ለማስወረድ እንደሚገደድ አስጠንቅቋል፡፡ የካንሰር ታማሚ የሆኑ ህጻናትን ጨምሮ፣ በየሳምንቱ በአማካይ 200 ታካሚዎችን ያለ ጊዜያቸው ሳያገግሙ እንደሚያሰናብት በመግለጽ፡፡
ለአገሪቱ መንግስት መዘጋት አንዳች መላ ካልተዘየደለት የሚደርሰው ምስቅልቅል መልከ ብዙ እንደሚሆን የሚናገረው የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ፣ ብሄራዊ የጤና ኢንስቲቲዩት ለህክምና ሙከራዎች አዳዲስ ታማሚዎችን መቀበል ሊያቆም እንደሚችል ይጠቁማል፡፡ የመሬት አስተዳደር ቢሮም በህዝብ ቦታዎች ላይ የነዳጅ ዘይት ፍለጋ ለሚያከናውኑ ኩባንያዎች ፍቃድ መስጠቱን ሊያቋርጥ እንደሚችል፣ ልዕለ ሃያሏን አሜሪካ፣ ኢኮኖሚዋንና ህዝቦቿን፣ አልፎ ተርፎም ተስፋ አድርገው የተጠጓትን ስደተኞች ክፉኛ የሚጎዱ ብዙ፣ እጅግ ብዙ ነገሮች ሊሆኑ እንደሚችሉም ያትታል፡፡
Source: http://www.addisadmassnews.com/
 
መግለጫ እስኪሰጥ ህዝቡ በትዕግስት ይጠባበቅ”
ስለመስቀሉ ከሰማይ መውረድ በጀመሪያ መረጃው እንዴት ነው የደረሳችሁ?
መስቀሉ ከሰማይ ወረደ ስለሚባለው የሻለ መረጃ የምታገኙት ወረደ ከተባለበት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮች ነው። እኛ ከሰማይ ወረደ ከተባለ ከቀናት በኋላ ነው በስፍራው የተገኘነው፡፡ ስለዚህ እነሱ እንደነገሩን እንጂ አይተናል ሰምተናል ብለን አይደለም መረጃ የምንሰጣችሁ፡፡
እነሱ ግን እንዴት እንደወረደ አይተናል ስላሉ መረጃውን ከእነሱ ነው ያገኘነው፡፡ ከእነሱ የተነገረን
እንግዲህ ነሐሴ 23 ለ24 አጥቢያ ሌሊት እንደወረደ ነው፡፡ ነሐሴ 23 የቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ክብረ በአል ነው፡፡ ጽላቷም ከቅዱስ ገብርኤል ጋር በተደራቢነት አለ፡፡ ሌሊት ማህሌት ቆመን ሳለ ከፍተኛ ድምጽ ተሰማ ነው የሚሉን፡፡ ተደናግጠን ስንወጣ ወደ ቤተልሄሙ አካባቢ መስቀሉ ወድቆ የሚንቦገቦግ ብርሃን አየን ነው ያሉት፡፡ ወዲያውኑ ሲነጋ እንዳንነካ ፈርተን ማንሳትም አልቻልንም፤ ነገር ግን በወቅቱ ዝናብ ስለነበር እዚያው ላይ መስቀሉ ሳይነሳ ድንኳን ተከልንበት ነው ያሉን፡፡ የታቦት መጐናፀፊያ ለማልበስም ወደ መስቀሉ ሳንቀርብ፣ ወርውረን አለበስነው ብለውናል፡፡ እኛ ነሐሴ 24 ወዲያውኑ ከሰአት ነበር የሄድነው፡፡ ስንሄድ ከባድ ዝናብ ስለዘነበና ቦታውም በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ መድረስ አልቻንም፤ ተመለስን፡፡ በ25 እንዲሁ ጥረት አድርገን ነበር፡፡ አልተሳካም። ነገር ግን በ27 ከሰዓት በኋላ ሄድን፡፡ መንገዱ እጅግ ፈታኝና በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ነው እንጂ መንገዱ ከአቅሜ በላይ ነበር፤ ነገር ግን ሊቀጳጳሱ ካልመጡ ለማንሳት እንቸገራለን ስላሉ እንደምንም ቦታው ደረስን።
ህዝቡም በጣም ይጐርፍ ነበር፡፡ ፀጥታ አስከባሪዎችም በብዛት ነበሩ፡፡ ወደ 10 ሰአት አካባቢ ደረስን፡፡ የት ነው ያለው አልናቸው። ወደ ድንኳኑ መሩን፡፡ መሬት ላይ ወድቆ ተመለከትነው፡፡
በወቅቱ ከመሬቱ ላይ እንዲነሳ እነሱ ብዙም ፍቃደኞች አልነበሩም፡፡ እዚያው ላይ እያለ ቤተክርስቲያን እንዲሠራለት ነው የፈለጉት፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን የሚሰራለት ከሆነም መስቀሉ መሬት ላይ ሆኖ አይደለም የሚቆፈረውና የግድ ወደመቅደሱ መግባት አለበት አልናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቃድ ከሆነ ለወደፊት ሊሠራ ይችላል ብለናቸው ውዳሴ ማርያም ደግመን የሚገባውን ፀሎት ከካህናቱ ጋር አደረስን፡፡ ከዚያም ወደ ድንኳኑ ገብተን መስቀሉን አነሳን። መጀመሪያ እኔ ነበርኩ መስቀሉን ያነሳሁት። ከዚያም ሰባኪያኑ እንዲይዙት አድርገን ቤተክርስቲያኑ አንድ ጊዜ ዞረን፣ ወደ መንበረ ታቦቱ እንዲገባ አደረግን፡፡ እስካሁን እንግዲህ ይህ ነው ያለው ሂደት፡፡
መስቀሉ ሲነሳ ብርሃናማና የሚያቃጥል ነበረ፣ ብዙ ተአምራቶችም ታይተዋል ተብሏል? በእርግጥ እነዚህ ነገሮች ነበሩ?
ያቃጥል ነበር የሚለው እንደው የሚያቃጥል ቢሆን ኖሮ መቼ እናነሳው ነበር፤ አናነሳውም። እኔ እንደዛ መስሎኝም ነበር የሄድኩት እንጂ መነኮሳቱ ማንሳት ይችሉ ነበር፡፡ የሚያቃጥል ነበረ፣ የሚበራ ነበረ ምናልባት ጨለማ ሲሆን ታይቶ ይሆናል እንጂ እኛ ምንም አላየንም፡፡
ወርቃማና የሚያንፀባርቅ ነው የተባለ ነውስ?
እንግዲህ ወደፊት ስለመስቀሉ በስፋት የሚገለጽ ይሆናል፡፡ ሰዎችም በተለያዩ መንገዶች ስለመስቀሉ እየጠየቁን ነው ጉዳዩን ለሲኖዶሱ አቅርበን፣ ሲኖዶሱ የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብለን ያለውን ነገር እንገልፃለን፡፡ እንግዲህ አሁን ህዝጀ ምዕመኑ ግማሹ ያለውን ነገር ተቀብሎ ይሄዳል ግማሹ ደግሞ እንዲሁ ለማታለል ነው ይላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ህዝቡ ግራ የተጋባ በመሆኑ የግድ ሀገ ስብከታችን ሰፋ ያለ መግለጫ የሚሠጥበት ይሆናል፡፡ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ስለሆነም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የግድ ያስፈልጋል፡፡ እዚያ ካሉ ሰዎች ጋርም ሰሞኑን እየተነጋገርንበት ነው፡፡
መስቀሉ በቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ባላገኘበት ሁኔታ ፎቶግራፉን በ10 ብር ለሽያጭ ማቅረብና ገቢ ማሰባሰብ አግባብ ነው?
እንግዲህ ይሄን የመሳሰለውን ጉዳይ ለማስተካከል ከቤተክርስቲያኑ አስተዳደሮች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ? ቤተክህነት እውቅና ሳይሰጠው ቀድሞ ህዝቡ እውቅና ይሰጠዋል፡፡ እኔ ሄጄ በነበረ ጊዜ ስለመስቀሉ አስተያየት ብሰጥ ኖሮ ምን አይነት ትርምስ ይፈጠር እንደነበረ ትገነዘቡታላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ ለወደፊት በስፋት ትምህርት እንዲሰጥ ጥረት ይደረጋል፡፡ የቋሚ ሲኖዶሱ የሚሰጠው ልዩ መመሪያ ይኖራል፤ ከዚያ በኋላ መግለጫ ይሰጥበት ሲባል በኋላ መረጃ በስፋት ይሰጣል፡፡
ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ተአምራት ታይተዋል ይባላል፡፡ ለእነዚህ ተአምራት እውቅና የሚሰጠው የትኛው አካል ነው?
ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡
ሲኖዶሱ ካልሰጠ ተቀባይነት አይኖረውም?
አዎ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ መስቀሉም ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሣኔ ካልሰጠ ተቀባይነት የለውም። በመሠረቱ መስቀሉ ያቃጥላል፣ ይፋጃል የሚባለው ሃሰት ነው፤ መስቀል ይፈውሳል እንጂ አያቃጥልም፡፡ እንዲህ ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ለወደፊት በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህ ላይ ሲኖዶሱ መቼ ነው ውሣኔ የሚያሳልፈው?
እንግዲህ ዛሬ ከሰአት የቤተክርስቲያኗን አስተዳዳሪዎች ጠርተናቸዋል (ይህ ቃለ ምልልስ የተደረገው ማክሰኞ ጠዋት ነው) ቅዱስ ሲኖዶሱ መረጃ ከነሱ ይጠይቃል፤ ከምን ተነስተው እንደዚህ እንዳሉ ከዚያ በኋላ ጉዳዩ በውይይት እስኪታይ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ በዚህን ጊዜ ውሣኔ ይተላለፍበታል ብሎ ለመናገር አሁን አይቻልም፡፡
መስቀሉን ብፁዕነትዎ ሄደው ተመልክተውታል፡፡ ታዲያ ስለመስቀሉ በእርግጠኝነት መናገር እንዴት አይቻልም? ፓትርያርኩም ባሉበት ነው የሚታየው ብላችኋል?
ፓትሪያርኩ እሄዳለሁ አላሉም እስከመጨረሻውም ላይሄዱ ይችላሉ፡፡ አይደለም እሣቸው እኔም ላልሄድ እችል ይሆናል፡፡ ፓትርያሪኩ ውሣኔ የሚያስተላልፉ ከሆነም በየደረጃው ያሉ ፈፃሚዎች ጉዳዩን የሚከታተሉት ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ብዙ መናገሩ ለስህተት ይዳርጋል፡፡ እንዳልኳችሁ የቋሚ ሲኖዶሱ ውሣኔ ይጠበቃል፡፡
ቢያንስ በስልጣን ደረጃ እርስዎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጻጳስ ነዎት፡፡ መስቀል ወርዷል ተብሎ ፎቶግራፉ ለሽያጭ ሲቀርብ ዝም ብሎ መመልከቱ ተገቢ ነው? ገንዘቡስ በምን ሞዴል ነው ገቢ የሚሆነው?
ሞዴልማ አድባራቱ ሁሉ አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያናችን መመሪያ መሠረት፣ የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ወሳኝ አካል ነው፤ ቤተክርስቲያኗን ወክሎ ይከሳል፣ ይከሰሳል ውል ይዋዋላል፣ የልማት ስራ ይሰራል፡፡ ስለዚህ ሰበካ ጉባኤው ሙሉ ስልጣን አላቸው፡፡ ስርቆትና ማጭበርበር ተፈፀመ የሚባል ከሆነ አጣሪ አካል ሄዶ ነው ሪፖርቱ የሚመጣው፡፡ ነገር ግን የትኛውም ቤተክርስቲያን በተቀመጠለት የአሰራር መመሪያ ገንዘብ የመሰብሰብ መብት አለው፡፡ ይሄ መስቀልም ሰበካ ጉባኤው ወስኖ ፎቶግራፉ 10 ብር ወይም 5 ብር እየተሸጠ ለህዝቡ ይሰራጭ ብሎ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ በትክክልም በዚህ መል/መ ገቢው ለቤተክርስቲያኑ ከሆነ ህጋዊ አሠራር ነው፡፡
ወረደ የተባለው መስቀል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምትጠቀማቸው የመስቀል አይነት አይደለም የሚሉ አስተያየቶችም እየተሠነዘሩ ነው…
እንግዲህ ስለመስቀሉ አሁን ዝርዝር ነገር መናገር አልችልም፡፡ በእርግጥ ከሠማይ ወርዷል? የማን መስቀል ነው? ከየት የመጣ ነው? የሚለው ከቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሣኔ በኋላ እንገልፃለን፡፡ ውሸት ሆኖ ከተገኘም ሠዎቹ ተጠያቂ ሊሆኑበት ይችላል፡፡
እርስዎ መስቀሉን ከተመለከቱት ይሄ የኦርቶዶክስ ነው አይደለም ለማለት እንዴት ከበድዎት?
እንደነገርኳችሁ የአንድ ሠው አስተያየት ተገቢ አይደለም፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሡ መስቀሉን አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ የሚሠጠው ውሣኔ የግድ ነው። ለነገሩ መስቀል መስቀል ነው፤ ይሄ የእገሌ ነው ያ የእኔ ነው የሚባል አይደለም፡፡ እንግዲህ መስቀሉ ላይ የሥነ ስቅለት ምስል አለበት፡፡ ይሄ አሣሣል የኛ የኦርቶዶክሣያውያን አይደለም የሚለውን የሲኖዶሡ ውሣኔ የሚያረጋግጠው ይሆናል፡፡ ሲኖዶሡ ውሣኔ እንሠጣለን እያለ በዋዜማው እኔ ሌላ ነገር ብናገር አግባብ አይሆንም፡፡ ህዝቡንም ያምታታል፡፡
ለህዝቡ የሚያስተላልፉት መመሪያ ካለ?
እንግዲህ ይሄ በኛ ሃገር ብቻ አይደለም የሚፈጠረው፡፡ በግብፅ (ዘይቱና) እመቤታችን ታየች ተብሎ እኔም አይቸዋለሁ፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ በሩሲያም ሠማይ ላይ ትልቅ መስቀል ተስሎ ታየ ተብሎ በየሚዲያው ሲነገር የሩስያ ቤተክርስቲያን መግለጫ ስትሠጥበት ነበር፡፡ እና ይሄ በኛ ብቻ ሣይሆን በሁሉም ያለ ነውና ህዝቡ እውነታውን ለማወቅ መታገስ አለበት። ሲኖዶሡ መግለጫ ቢሠጥበት እንኳ ሁሉም ህዝብ በእኩል አረዳድ አይረዳውም፡፡ ግማሹ ተአምር ነው ሊል ይችላል፡፡ ሌላው አይደለም ሊል ይችላል። ለማንኛውም ከቅዱስ ሲኖዶሡ ውሣኔ በኋላ በየሚዲያው መግለጫ የሚሠጥበት ይሆናል፡፡ ህዝቡ ሲኖዶሡ ውሣኔ እስኪሠጥበት ድረስ “ይሄ ነው ያ ነው” ሣይል፣ ተረጋግቶ የራሱን ትችትና ውሣኔ ሣይጨምርበት እንዲጠብቅ እንጠይቃለን፡፡
ውሣኔው በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃንና በየቤተክርስቲያኑ የሚሠጥ ይሆናል፡፡ እስከዚያው መታገስ ያስፈልጋል፡፡
Source: http://www.addisadmassnews.com/
 
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ አመትና የሁሉም የምህንድስና ዘርፍ ተማሪዎች ከትላንት በስቲያ ከግቢ መባረራቸውን የአዲስ አድማስ ምንጮች ገለፁ፡፡ ለተማሪዎቹና ለዩኒቨርሲቲው ግጭት ምክንያት የሆነው የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሆነም ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡
የሁሉም የምህንድስና ተማሪዎች አራተኛ አመት ላይ ሲደርሱ የብቃት ምዘና ፈተና ይወስዳሉ ያሉት ምንጮቹ፣ የዘንድሮው ተማሪዎች ግን ለእረፍት ወደየቤታቸው ሲሄዱ ሞጁል ይዘው ሄደው አጥንተው መፈተን ሲገባቸው፣ ድንገት ተፈተኑ መባላቸው እንዳስደነገጣቸው ገልፀዋል፡፡

“የሁለት ቀን ትምህርት ተሰጥቷችሁ ተፈተኑ መባላችን ትክክል አይደለም” ያለችው አንዲት የዩኒቨርስቲው ተማሪ፤ “ከእኛ በፊት የነበሩት የአራተኛ አመት ተማሪዎች ሳይፈተኑ “Holistic pass” (ምዘናውን እንዳለፉ የሚልጽ) ወረቀት እንደተሰጣቸው እናውቃለን” ብላለች፡፡
የብቃት ምዘና ፈተናው የሚጀምረው ካለፈው አመት ተማሪዎች እንደነበር የገለፀችው ተማሪዋ፤ ዘንድሮ ከእኛ መጀመሩ አግባብ አይደለም፣ ቢጀመርም ከልምምድ በኋላ እንዲሆን ጠይቀን ምላሽ አላገኘንም ብላለች፡፡
“እኛ አንፈተንም አላልንም ግን የሶስት አመት ትምህርት በሁለት ቀን ቲቶር ለፈተና አያበቃም” ያለው ሌላው ተማሪ፤ የፈተናው ጊዜ ይራዘምልን ብለው በመጠየቃቸው “ብትፈተኑ ተፈተኑ ያለበለዚያ ግቢውን ልቀቁ” ተብለው በፖሊስ ሃይል ከግቢ መባረራቸውን ገልጿል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከሶስት ሺህ በላይ ተማሪዎች ከግቢው እንደተባረሩና በአርባ ምንጭ ከተማ ሲቀበላ በተባለው አካባቢ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ግቢ ብዙ ተማሪ እንደሚገኝ የተናገረው የሲቪል ምህንድስና የአራተኛ ዓመት ተማሪ፤ ሌሎቹም በመስጊድና በየአስፓልቱ ላይ እየተንገላቱ እንደሆነ ገልጿል፡፡
“ያለ ምግብና ያለ መጠለያ በረሃብ ልናልቅ ነው” ያለው ሌላው ተማሪ፣ መንግስት በአስቸኳይ ለጉዳዩ እልባት ይስጥልን ሲል ተማጥኗል፡፡ ከአራተኛ አመት ተማሪዎች በተጨማሪ የአምስተኛ አመት የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎችም መባረራቸውን የጠቀሰው ተማሪው፤ ሳናጠና እና ሞጁል ሳይዘጋጅ በሁለት ቀን የክፍል ጥናት ብቻ የሶስት አመት ትምህርት ተምረን ውጤት ልናመጣ ስለማንችል ባንፈተን ይሻላል የሚል አቋም መያዛቸውን ተናግሯል፡፡
“ዩኒቨርስቲው ሃላፊዎቹ የሚሏችሁን ሰምታችሁ ካልተፈተናችሁ ምንም አይነት አገልግሎት ከግቢው አታገኙም በሚል በፖሊስ ሃይል ተባረናል” ያለው ይሄው ተማሪ፤ ወደ ቤተሰብ ለመመለስም ሆነ እዛው ከተማ ውስጥ አልጋ ይዞን ለመቆየት ምንም ገንዘብ እንደሌላቸው ጠቁሞ በችግር ላይ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ ትላንትና ረፋድ ላይ በከተማው ፖሊስ ጣቢያ የመሰብሰቢያ አዳራሽ “ተሰብሰቡና እንነጋገር” የሚል ሃሳብ ከዩኒቨርሲቲው ሰዎች ቀርቦ ተማሪዎች አዳራሹን ሞልተው፣ ሃላፊዎቹን ለረጅም ሰዓት ቢጠባበቁም ማንም እንዳልመጣና በመጨረሻም ተማሪዎች መበታተናቸውን ምንጮች ገልፀዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለምህንድስና ተቋሙ ፕሬዚዳንት ለዶ/ር ካሳሁን እና ለዩኒቨርስቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ሃላፊ ለዶ/ር ተሾመ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ልናገኛው አልቻልንም በዩኒቨርስቲው የተለያዩ የቢሮ ስልኮች ደውለን ጉዳዩን ለማጣራት ያደረግነው ጥረትም ስልኮቹ ባለመነሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
Source: http://www.addisadmassnews.com/
 
| Copyright © 2013 Lomiy Blog