“በበዓሉ ግርማ ጉዳይ ላይ ከሕሊና ዕዳ ነጻ ነኝ” ደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ

asfaw_damte
ደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ ናደው፣ የተወለዱት መጋቢት 1ዐ ቀን 1927 ዓ.ም. አዲስ አበባ ጊዮርጊስ አካባቢ፣ መርሐ ጥበብ
ማተሚያ ቤት ግቢ ከሚባለው ቦታ ነው፡፡
አቶ አስፋው የቤተ ክህነት ትምህርት ለጥቂት ጊዜ ከተማሩ በኋላ፣ በዘመናዊ ትምህርት፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃን፣ በኮከበ
ፅባሕ ቀ.ኃ.ሥ. አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ በመጀመሪያ ዲግሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሁለተኛ ዲግሪ ደግሞ
በእንግሊዙ ኪምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተምረው ተመርቀዋል፡፡
ወደሥራ ዓለም ከተቀላቀሉ በኋላ፣አብዛኛውን የሥራ ጊዜያቸው በገንዘብ ሚኒስቴር በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ያገለገሉ ሲሆን፣
ከገንዘብ ሚኒስቴር እንደለቀቁ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ድርጅትና በኩራዝ አሳታሚ ሠርተዋል፡፡
አቶ አስፋው ከኢትዮጵያ ውጭ ካሳለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ፣ በእንግሊዝ ለትምህርት ሶስት ዓመት፣ ቀሪውን አራት ዓመት
ደግሞ በአሜሪካ በሥራ ነበር::

በድርሰቱ ዓለምም፣ “አንድ ለአምስት” የተሰኘ ረጅም ልቦለድ ያበረከቱ ሲሆን፣ በደራሲያን ማኀበር ካሳተመው በ“የዘመነ
ቀለማት” መፍሐፍ ላይ በአጫጭር ግጥሞቻቸው፣ በ‹‹እነሆ››መድብል ደግሞ በአጫጭር ታሪኮች ተሳትፈዋል፡፡ከዚህም
በተጨማሪ ከ1970 እስከ 90ዎቹ ዓመታት ድረስ ስለ አማርኛ ጥበበ ቃላት አንዳንድ ነጥቦችን ከስር ጀምረው መጣጥፎችን

አበርክተዋል፡፡
ደራሲና ሐያሲ አቶ አስፋው ዳምጤን የረጅም ጊዜ ጓደኛቸው ከነበረውና የደርግ ጅቦች ሰለባ ከሆነው ታዋቂውና ተወዳጁ ደራሲ
በዓሉ ግርማ ከሚወደው ሕዝብ ጋር የመጨረሻው በነበረችው ምሽት ከአቶ አስፋው ዳምቴ ጋር በሰላም አብረው ከተዝናኑ
በኋላ ፣ተሰነባብተው ሌላ ታሪክ እስኪፈጠር ድረስ፣በአንዲት ግሮሰሪ ደጅ ላይ አብረው አብረው ነበሩ፣
መጽሔታችንም “ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የቀበረ” እንደሚባለው፣ስለበዓሉ ግርማ የመጨረሻዋ ምሽት በዝርዝር
እንዲነግሩን አቶ አስፋው ዳምጤን ጋብዘናቸዋልና እነሆ::
bealu-girma1ፍቱን፦- የደራሲ በዓሉ ግርማ ባለቤት፣ ወ/ሮ አልማዝ አበራ፣ ‹‹…የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም. ቀን ላይ አስፋው ዳምጤ
እቤት ስልክ ደወለ :: በዓሉ ቤት አልነበረምና፣ ስልኩን አንሥቼ ያነጋገርኩት እኔ ነበርኩ :: የእግዜር ሰላምታ ከተለዋወጥን
በኋላ፣ ‹… በዓሉ እንደመጣ እዚያ እቀጠሯችን ቦታ ባስቸኳይ እንድትመጣ ብሎሃል በዪልኝ …› ብሎ ስልኩን ዘጋ ::››
ብለዋል:: እውነት ነው ?

አቶ አስፋው፦ የዚህ አጭር መልሱ ‹ሐሰት ነው› ነው:: ይኸንኑ መልስ ለሚያዚያ 8 ቀን ውንጀላቸው፣ በሚያዝያ 15 ቀን
1989 እፎይታ ጋዜጣ ላይ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት ሰጥቼያለሁ ::
በዚያው ወቅት ስለዚያች ዕለት የበዓሉ ከቤት አወጣጥ ፣ Black Lions (ብላክ ላየንስ) የተባለ፣ የበርካታ ኢትዮጳውያን
ደራስያንን የሕይወት ታሪክ እና ሥራዎ ቻቸውን ለማስተዋወቅ የሚጥር መጽሐፍ ደራሲ፣ ሞልቬር፣ እርሳቸዉ ነገሩኝ ብሎ
የጻፈው፣ አንድ ጓደኛው እቤቱ መጥቶ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ እርሳቸው አንድ መጥፎ ነገር ይሆናል የሚል ስሜት
ተሰምቷቸው መሔዱን ቢቃወሙም ይዞት ሔደ፤ በዚያውም ቀረ የሚል ነው::
እንግዲህ ስለ እዛች ዕለት ከቤት አወጣጡ የቀረበው መረጃ የተጋጨ ስለሆነ ወይ ስልክ ደውሎ ጠራውና ሔደ ወይም
መጥቶ ይዞት ሔደ ይበሉ፣ አንዱን ይምረጡ የሚል ነበር የኔ የዚያን ወቅት ጥያቄ::
ሐቁ ግን፣ በዚያች ዕለት እንዳጋጣሚ ሆኖ፣ ስልክ አልደወልኩለትም፣ ቤቱም አልሔድኩም ነበር:: ምክንያቱም፣ የአዲስ አበባ
ክልልን የዐሥር ዓመት የአብዮት ታሪክ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ ተሳታፊ በመደረጌ፣ የሥራ ውጥረት ገጥሞኝ አመሽ ስለ
ነበረ ነበር::
በዚያችው ምሽት ግን፣ ስድሰት ኪሎ በሚገኘው በአዲስ አበባ ኢሠፓአኮ በስብሰባ ቢሮ ሌሎቹ ከሔዱም በኋላ አመሻሽቼ
ወደ ቤቴ ስጓዝ ማምሻ ቦታችን አካባቢ ስደርስ፣ ‹ለመንገድ› ለማለት በተለመደችው ቦታችን ለማቆም አዙሬ አቆምኩ:: አንድ
ወጥ ጽሑፍ ለማቀናበር እንድንችል በቀረቡልን የየቀበሌ፣ ከፍተኛ፣ ቃጣና እና የተቋማት የ10 ዓመታት የታሪክ ዘገባ
መረጃዎች ጭንቅላቴ ተሞልቶና ስቆዝም ቆየሁ:: ወደ ሦስት ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል ፣ የበዓሉን የመኪና ክላክስ ሰምቼ ዞር
ስል፣ መኪናው ውስጥ አየሁት:: የመጣበት አግጣጫ የቤቱ ስላልነበረ፣ የት እንዳመሸ ገመትኩ:: መኪናዋን ባለችበት ትቶ፣
በእግሩ መንገዱን ረጋ ብሎ አቋርጦ መጣና እኔ መኪና ውስጥ ገባ:: ብዙም የረባ ነገር የምናወራው ስላልነበረን ይሆናል ትዝ
የሚለኝ የለም:: እንደኔው ደከም ያለው መሰለኝ:: ካሰብኩት በላይ በመቆየቴና እሱም የሚሔደው ወደ ቤቱ ስለነበር ብዙ
አልቆየንም:: ሃያ ቢበዛ ሠላሳ ደቂቃ ቢሆን ነው:: መኪናዬን አዙሬ መኪናው ጎን አቁሜለት ሲወርድ እኔ ወደፊቴ ቀጠልኩ::
እየተጠባብቅን አልነበረም የምንሔደው ሁሌም ቢሆን::
ስለዚህ፣ ተቀጣጥረን ሳይሆን በእንደዚያ ዐይነት አጋጣሚ ግን ተገናኝተን ነበር ያችን ዕለት::
አሁን ደግሞ በአበራ ለማ በተበተነው የ16 ገጽ ሐተታ ውስጥ በገጽ 6 ላይ ጓድ ቁጥር ኀምሳ ሦስት ከተሰኘ ባለሥልጣን፣
‹‹…ወደ ማታ በዓሉን የደህንነት ሰዎች ይዘውት እንደሄዱ ከቤተሰቡ ሰማሁ…›› የሚል ባለቤቲቱን ያይን ምስክርነት የሚሰጡ
የሚያስመስላቸው ‹መረጃ› ያስነብበናል:: ምን ማለት ነው; በእርግጥ ባለቤቲቱ ለባለ ሥልጣኑ ይኸን መረጃ ሰጥተዋል ሊለን
ነው ዐላማው; ሞኙ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ ሆነበትሳ !
ፍቱን፦ በዓሉ እርሶ ጋ ከመድረሱ በፊት የት ቆየ ብለው ነበር የገመቱት?
አቶ አስፋው፦ ጥቂት ቀደም ብሎ እዚያው አካባቢ ወዳጅ እንደነበረው ተገንዝቤ ነበር ::
ፍቱን፦ የማን ቤት ነው ?
አቶ አስፋው፦ እሱን አላውቅም ::
ፍቱን፦ ወንድ ሴት?
አቶ አስፋው፦ ሴት::
ፍቱን፤ በዚያች ዕለት ምሽት እዚያ ቆይቶ ከተመለሰ በኋላ ነበር ከእርሶ ጋር የተገናኛችሁት?
አቶ አስፋው፦ እንደዚያ ነበር አመጣጡን ሳይ የገመትኩት::
ፍቱን፦ የቅርብ ጓደኛ እንደመሆንዎ ምናልባት ለመምከርም ለመገሠጽም አልሞከሩም?
አቶ አስፋው፦ በአዘቦቱ ከምንወያይባቸው ርእሰ ጉዳዮች ውጭ ነበረ:: የእኔና የርሱ ቁልፍ ጉዳይ ድርሰትንና ተዛማጅ
ጉዳዮችን የሚመለከት እንጂ ሌላውን የሕይወቱን ክፍል የግሉ ብቻ አድርጌ ነበር የማየው:: ከዚያ ያለፈ ነገር እርሱ
በአጋጣሚ በሚያነሣቸው ጉዳዮች ነው የምናተኩረውና ይኸ ተነሥቶ አያውቅም፡፡
ፍቱን ፦ እርሶና በዓሉ በየሳምንቱ ሮብ ካልሆነ ኀሙስ አለዚያ ዐርብ ትገናኙ የነበረበት የተለየ ምክንያት ነበራችሁ?
አቶ አስፋው፦ አዎን፤ እኔንና እርሱን የሚመለከት ትንሽ የግል ጉዳይ ነበረች::
ፍቱን፦ አሁን መግለጽ አይፈልጉም?
አቶ አስፋው፦ ከዋናው ጉዳያችን ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሌለውና ለማንም የሚጠቅም (ወይም የሚጎዳ) መረጃ አይደለም::
ግን የግል ነገር ነው::
ፍቱን ፦በዚያች ምሽት ስንት ሰዓት ላይ ተገናኛችሁ?
አቶ አስፋው፦ ወደ ሦስት ሠዓት ግድም ነው :: በትክክል አላሳተውስም ::
ፍቱን፦ የዚያን ምሽት የበዓሉ አለባበስ እንዴት ነበር?
አስፋው፡- እንደ ሁሌውም ሽቅርቅር ያለ ነበር ማለት ይቻላል:: ቡላ ቀለም የሆነ ሙሉ ልብስ መሰለኝ:: ልብ ብዬ
ያተኩርኩበት አልነበረም:: ዐይኑ ላይ ኦይንትመንት ብጤ ያየሁ መስሎኛል::
ፍቱን፦ ድካም ያዩበት ለምን ይመስልዎታል?
አቶ አስፋው፦ እንደርሱ ንቁ የሆነ ተንቀሳቃሽና በሥራ ውጥረት ውስጥ የቆየ ሰው ያለ ፈታኝ ሥራ ውሎ ሲያመሽ ይህ
ዐይነት ስሜት የሚያድርበት ይመስለኛል:: ጊዜውም እየተማሸ በመሔድ ላይ መሆኑን ማሰብ ይኖርብናል:: የኔም መንፈስ
ብዙ የነቃ መሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም:: በውሎዬ ስላጋጠሙኝ አንዳንድ መንፈስ መሳጭ ስሜት ቀስቀሽ ስለሆኑ የቀበሌና
የከፍተኛ የታሪክ ሰነዶችና መረጃዎች እርሱ ከነበረበት ሁኔታ ለመወያያ አመቺ አልነበሩና የሚነሡ አልነበሩም ከርሱ ጋር::
ፍቱን፦ ከበዓሉ ሁኔታ ወይም ከአካባቢው የታዘቡት የተለየ ነገር ነበር?
አቶ አስፋው፦ ምንም የታዘብኩት ነገር አልነበረም:: መኪናዬን ሲያይ ምንም ሳይል ዐልፎኝ መሔድ ስለማይችል መጣ
እንጂ ጊዜው ለተለምዶው ዐይነት
ውይይት አመቺ ሆኖ አልነበረም የመጣው:: እንዳልኩህ ያኔ ሰዓቱ ሁለታችንም ወደየቤታችን ለመሔድ መንፈሳችን
ያዘነበለበት ሁኔታ ነበር::
ፍቱን፦ ስንት ሰዓት አካባቢ ተንቀሳቀሳችሁ?
አቶ አስፋው፦ ከሦስት ሠዓት ቢያልፍም ብዙ አይመስለኝም::
ፍቱን፡- ስትለያዩ፣ በዓሉ ወዴት እንደሚሔድ ያውቁ ነበር?
አቶ አስፋው፦ ወደ ቤቱ ነዋ! የእኔን መኪና አይቶ የቆመው ወደ ቤቱ አግጣጫ እየነዳ ሳለ ነበር:: መኪናው ዘንድ ሳደርሰው
ጉዞውን ነው የሚቀጥለው:: ለእኛ ያቺ ምሽት እንደሌሎቹ ሁሉ አንድ ሌላ ምሽት ነበረች! ከመምጣቱ ዐምስት
ደቂቃዎች ቀደም ብዬ ሔጄ ቢሆን ኖሮ፣ በዚያች ማታ አንተያይም ነበር::
ፍቱን፦ የበዓሉን መሰወር የሰሙት በምን ሁኔታ ላይ ሆነው ነበር?
አቶ አስፋው፦ በማግሥቱ ጧት ወደ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ ነበር:: ወደ አዲስ አበባ ኢሠፓአኮ ለመሔድ እየተደራጀሁ
ሳለ፣ ባለቤቱ ደወለችልኝ ::
ፍቱን፦ወ/ሮ አልማዝ፣‹‹በዓሉ የማታ ማታ ወደቤት ይመለሳል ብዬ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ብጠብቅም የውሃ ሽታ
እንደሆነ ቀረ፡፡ ቢቸግረኝ አስፋው ቤት ደወልኩ፡፡ ሚስቱ ስልኩን አነሳች፡፡ ’…አስፋው እቤት ገብቷል?…’ ስል ጠየቅኋት፡፡
’…አዎን ገብቷል…’ አለችኝ፡፡ ይሄኔ ግራ በመጋባት፤ ’…ባሌን ከቤት ጠርቶ ወስዶት የት ጥሎት ነው እሱ ተቤቱ የገባው?…’
እያልኩ አፋጠጥኳት፡፡ ቀጥዬም ’እስኪ አቅርቢልኝና ላናግረው…’ ስላት፤ ’የገባ ምስሎኝ ነበር እንጂ አልገባም’ ብላ
የመጀመሪያ ቃልዋን አጠፈችብኝ፡፡ የስልክ ንግግራችንም በዚሁ ተቋጨ›› ብለዋል እውነት ነው?
አቶ አስፋው፦ ሐሰት ነው
ፍቱን፦ መሥረያ ቤት ነበር የደወሉት?
አቶ አስፋው፦ አዎን፣ ኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት እኮ ነው ! እዚያኛውማ ገና ልሔድ ነው ::
ከዚያ፣ ‹‹በዓሉ እኮ ትላንት ማታ አልገባም:: አልተገናችሁም ነበር ወይ;›› ስትለኝ ያመሸበት ትዝ ብሎኝ ነበርና፣ ‹‹አይቸዋለሁ፣
ግን›› ብዬ የምለው ጠፋኝና፣ ‹‹አሁን የምሔደው አንድ ትልቅ ባለሥልጣን ዘንድ ለስብሰባ እንዲህ ዐይነቱን ነገር ለማጣራት
ችሎታ አለው:: በከተማው ውስጥ የሚካሔደው ነገር ሁሉ የሚዘገብለት እርሱ ስለሆነ አነጋግሬ ሁኔታውን አጣራለሁ››
አልኳት:: አዲስ አበባ ኢሠፓአኮ ጽሕፈት ቤት እንደረስኩ በቀጥታ ወደ በላይ ኀላፊው ቢሮ ገብቼ ነገሩን አነሣሁ:: ‹‹አንድ
ቦታ (ጾታን ጠቁሞ) አድሮ ይሆናል ነገ ብቅ ይላል ››አለኝ አቃሎ:: እኔም ይኸ ሊሆን እንደማይችልና ማታ ከዚህ ወደ ቤቴ
ስሔድ እንደተገናኘንና ስንለያይ ወደ ቤቱ እያመራ እንደ ነበር አጠንክሬ ገለጽሁ:: ከዚያ፣ ቆይ ብሎ አንድ ቦታ ደውሎ ጥቂት
ከተነጋገረ በኋላ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ገለጸልውልኛል፣ አሁንም ጥቂት አሰብ አደረገና ሌላ ቦታ ደውሎ ተናጋገረ::
ውጤቱ ምንም ለውጥ አልነበረውም:: በዓሉን የሚያህል ሰው ጠፍቶ የአዲስ አበባን አጠቃላይ ሁኔታ የማወቅ ዐቅም ካለው
ከዚህ ቢሮ ተሰውሮ ብዙ እንደማይቆይ ተስፋ ያለኝ መሆኑን ተናግሬ ወደ ስብሰባ ቢሮው ሔድኩ ::
ፍቱን፦ ያ ባለሥልጣን ማን ነበር ?
አቶ አስፋው፦ ኮማንደር ለማ ጉተማ ነበር :: በትምህርት ቤት ዕውቂያ ስለነበረን ነው የሚቻለውን ያህል ሊጥርልኝ ይችላል
የሚል ተስፋ የነበረኝ ::
ፍቱን፦ ኮማንደር ለማ የት እና የት የደወሉ መሰለዎት?
አቶ አስፋው፦ ስለ አዲስ አበባ የየዕለት ሁኔታ የሚያሳውቁት አካላት ዘንድ ነው ብዬ ነበር የገምኩት::
ፍቱን፦ ደህንነት መሥሪያት ቤት ማለት ነው?
አቶ አስፋው፦ ሊሆን ይችላል:: ልዩ ክፍሎችም ሊኖሩት ይችላሉ፣ አላውቅም::
ፍቱን፦ ያንለት ወ/ሮ አልማዝን በድጋሚ አግኝተዋቸው ነበር?
አቶ አስፋው፦ አዎን፣ በስልክ ይሁን በግምባር፣ ምንም ፍንጭ ለጊዜው ባላገኝም፣ ተስፋ እንዳልቆረጥኩ ነግሬያት ነበር ::
ፍቱን፦ የበዓሉን መሰወር ጉዳይ እርስዎ የምር ነበር ያዩት ወይስ …?
አቶ አስፋው፦ አዎን ግን ደግሞ አንዳንድ የገለጻቸውን ሁኔታዎች የሚከርር አይሆን ይሆን የሚል ልብ ከፋይ ስሜት
መነሻው ላይ ልቤን ያሟግት ነበር:: ለምሳሌ፣ ቀደም ብሎ ባንድ ወቅት ታሰረ የሚል ወሬ ተነዝቶ ነበር:: ያን ወቅት ኢትዮጵያ
መጻሕፍት ድርጅት ድረስ ይመጣ በነበረበት ጊዜ፣ ልክ ከእኛ ዘንድ ተመልሶ እንደሔደ፣ አንድ ሰው ደውሎ ስለ መታሰሩ
ነገረኝ:: ግን፣ እኛ ዘንድ መጥቶ እንደነበርና ዝም ብሎ ወሬ ነው ማለቴን አስታውሳለሁ:: ከዚያ በኋላም እርሱው ከቤተ
መንግሥት አካባቢ ቤቱ ተደውሎ ስለ ደህንነቱ የተጠየቀ መሆኑን ነግሮኝ ነበር:: ሆኖም ሙሉ ለሙሉ መተማማን አስቸጋረ
ነበር:: ከኦሮማይ ጋር መያያዙ ታሳቢ ጉዳይ ስለሆነ ስለ ነገሩ ክብደት ማመን ፍጽም አልነበረም::
ፍቱን፦ መንግሥቱ ናቸው የደወሉት?
አቶ አስፋው፦ ማን እንደሆነ ተነግሮት እንደሁ አልነገረኝም:: እኔ ግን ሊሆን ይችላል ብዬ አላሰብኩም፣ አልመሰለኝም::
ፍቱን፦ ስለዚህ የምር ይሆናል ብለው አላሰቡትም ነበር?
አቶ አስፋው፦ አጽናኝነት ያላቸው ምልክቶች ሆነው ቢታዩም ቀላል አድርጎ የሚታይ ነገር አልነበረም :: እርግጥ መንፈስን
አዋዥቋል:: ከዚያ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ፈልጉ አፋልጉ የሚል ቴሌግራም እንደተበተነ ሰማሁ:: በዚያው ሰሞን
ከበዓሉ ጋር ቅርብ ግንኙነት አላቸው ተብለው ከታሰቡ ውስጥ ይመስለኛል ሦስት ሰዎች በተናጠል ተጠርተው ስለ ጉዳዩ
የሚጠረጥሩት ነገር እንዳለ እንዲጠቁሙ ፍንጭ ካገኙ ደውለው እንዲያሳውቁ ስልክ ቁጥር ተሰጣቸው :: ከሦስቱ ሁለቱ
ባለቤቱና እኔ ነበርን ::
ፍቱን፦ ማን ነበር የጠየቀዎ?
አቶ አስፋው፦ መልኩን እንጂ ስሙን አላውቀውም ::
ፍቱን፦ ወ/ሮ አልማዝ በርስዎ ላይ ቅያሜ ለምን ሊያድርባቸው ቻለ?
አቶ አስፋው፦ በዓሉ ከተሰወረ በርከት ያለ ቀናት ቆይቶ፣ ወ/ሮ አልማዝ ‹‹የበዓሉ መኪና ቃለቲ መንገድ ላይ ቆማለች አሉ፣
ሔደን እናምጣት›› አለችኝ ቤቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ደውላ :: ‹‹ይኸንማ ማድረግ አንችልም:: በተሰጠሸ ስልክ ቁጥር ደውለሽ
አሳውቂ እንጂ ከነረው ሁኔታ እንደፈለገን ማድረግ አንችልም ::››፣
ከዚያ በነገሯ ሁሉ የማላውቃት ሰው ዐይነት ሆነችብኝ:: ከመነሻው ብዙ ትውውቅም አግባብም አልነበረንም:: የኔ ጉዳይ
ከባዓሉና ከድርሰቱ ጋር እና በውጭ ነበር ::
ከሥራ ከታገደ በኋላ ቤቱ መሔድ ግድ ሆነ ፤ እኔና እርሱ መገናኘት የምንችልበት ዋና ቦታ ያ ብቻ ሆና ነው :: እርሱ ሳይኖር
ቤቱ ከማን ለመወያየት ነው እንድሔድ ይጠበቅ የነበረው:: ቀድሞም ቤት ለቤት የመጠያየቅ እና ያን ዐይነት ማኅበራዊ
ግንኙነት አልነበረንም :: ያኛው ለሁለታችንም ሌላ ዐውድ ነበር :: እርሱ የራሱ እኔም የራሴ ነው የነበረን::
ስለዚህ፤ ለዚህ እና ለተለያዩ የእርሷ ውንጀላዎችም ሆኑ ስሞታዎች
ትክክለኛው መልሱ የሚገኘው ከእኔና ከበዓሉ የግንኙነት ዐይነትና መሠረታዊ ባሕርይ ነው :: ነገር በመደጋገም አዲስ እውነት
አይፈልቅም:: ስለ እርሳቸው አመለካከት ትክክሉን ነገር ለማግኘት የምር ለማወቅ በየጊዜው የሰጧቸውን በርካታ ቃለ
መጠይቆች እያገናዘቡ ማንበብ ነው::
አሁን የተበተነውና መጽሔቶችን እያጣበበ ያለው ሰፊ ሐተታ ገሐድ ያወጣው ቁምነገር፣ ሚያዝያ 8 ቀን 1989 በወ/ሮ
አልማዝ ስም ከመነሻ የውንጀላ ጽሑፍ አንሥቶ ሐተታው ውስጥ በስማቸው የወጣው ሐሳብ ሁሉ ከነቃላቱ የእርሳቸው
እንዳልነበረ ነው :: ሰው ትኩረት እንዲሰጠው የበዓሉን ስም ሽፋን አድርጎ የራሱን ቂም፣ በቀልና እና ብሶት ለማሰተላለፊያ
የተጠቀመበት ሆኖ ነው የሚገኘው ጽሑፉን በታኙ :: እውነት ፈላጊ ፈልፍሎ እንደሚደርስበት ጥርጥር የለኝምና፣ ይኸኛውን
በዚህ ጨርሻለሁ::
ፍቱን፦ በዚህ ጉደይ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጠይቀው ያውቃሉ?
አቶ አስፋው፦ አልተጠየቅሁም:: የፍርድ ቤትን ፍጹም አሉቧልታ መች ይቋቋመዋል; ቀደም ሲል አሉቧልታን ይዞ ወደ
መገናኛ ብዙኃን መሔድ ይቀል ነበር:: አሁን ያ በር እየጠበበ ይመስለኛል::
ፍቱን፦ በእርስዎና በበዓሉ መካከል ቅያሜ ወይንም አነሥተኛ ቁርሾ ነበር?
አቶ አስፋው፦ የምን ቁርሾ አመጣህብኝ:: ቀድሞ መች ለበቂ ጊዜስ ተገናኝትን:: በጽሑፉ አድናቂው ነኝ ፤ ሒሳዊ ትችት
የሚጠላ ሰው አልነበረም:: በሙያና በመሥሪያ ቤት የተለያየን ነን:: ስለዚህ፣ ላልከው ነገር ሰበብም አልነበረም::
ፍቱን፦ ኩራዝ እንዲገቡ በዓሉ ከፍተኛ ውትወታ አድርጎ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው፣ ኋላ በምን የተለየ ምክንያት እዚያ
ገቡ?
አቶ አስፋው፦ ወደ ኩራዝ የመግባቱ ጥያቄ ረዘም ያለ የጊዜ ሒደት የነበረውና ከዚህ ቀደም መልስ የሰጠሁበት ነው:: በዚህ
ረገድ በዓሉ ከብዙዎች አንዱ ነበር::
ይሁንና፣ የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው ተስፋዬ አያሌው አንድ የጥበባት ጉዳይ መጽሔት
ለመመሥረት ተነሣሥቶ ከያለበት ጽሑፍ የሚያቀርቡ ሰዎች ሲያፈላልግ በዚያ ሳቢያ ተገናኝተን ተዋወቅን:: ከዚያ፣ ሥነ
ጽሑፍን ለማሳደግ ከልብህ ካሰብክ፣ አሰታሚ ዋና ክፍሉን አጠናክረህ ምራው ብሎ፣ ሊያሠራ የሚችል ሁኔታ
እንደሚያመቻችልኝ አሳመነኝ:: እኔም በኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት ላራት ዓመታት ያህል በተግባርም በንባብም
የቀሰምኩትን ዕውቀትና ልምድ ሰፋ ባለ መድረክ ተግባር ላይ ለማዋል አጓጓኝ:: ከባድ ውሳኔ እያደረግሁ መሆኔም እየተሰማኝ
ነበር :: ይሁን እንጂ ስበቱ አየለና፣ ተደራድሬ የአሳታሚ ዋና ክፍሉ ኃላፊ ሆኜ ተቀጥሬ ገባሁ::
ከ1977 እስከ 1983 የነበረውን የኩራዝ አሰታሚ ድርጅት እንቅስቃሴና ተጨባጭ ውጤት ሳሰተውል ያደረግሁት ትክክለኛ
ውሳኔ እንደነበረ እና በውጤቱም እርካታ ይሰማኛል::
ፍቱን፦ ወዳጅዎን የኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅት ባለቤት እንዴት አሳመኗቸው?
አቶ አስፋው፦ ከእርሱ ጋር ቀደም ሲል ከገንዘብ ሚኒስቴር ዘመኔ ጀምሮ ነበርና የምንተዋወቀው፣ ስለሁኔታዎች የጋራ
መግባባት ነበረን:: በዚያው ተወስኜ እስከ ዘለቄታው እንደማልቆይ አስቀድሞ የታወቀ ነበር:: ስለዚህ ለመልቀቅ ችግር
አልነበረም ::
ፍቱን፦ ለበዓሉ መሰወር ከኦሮማይ ሌላ መንሥኤ ይኖራል?
አቶ አስፋው፦ የግንኙነታችን አግጣጫ ሥነ ጽሑፍ አንድ ጠበብ ያለ ገጽታው ነው:: ከዚያ ውጭ ያለ ገጽታው ነው
የሚበልጠው፣ የሚሰፋው:: በዓሉ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረ በዚያ አግጫም ኃላፈነቶች ነበሩበት :: ስለዚህ ከቁንጽል
እይታ ተነሥቶ ትልቅ ድምዳሜ መድረስ አስቸጋሪ ነው::
ፍቱን፦ በእርሶ ላይ ከሚሰጡ አስተያየቶች መካከል አንዱ፣ አቶ አስፋው ሰኔና ሰኞ የሚባለው ገጥሞባቸው ነው እንጂ ፣
ጓደኛቸውን አሳልፈው የሚሰጥ ሰብእና የላቸውም የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ አቶ አስፋው ጓደኛቸውን የሚሸጡ
ሰው አይደሉም፣ ነገር ግን፣ የዚያች ዕለት ምሽት ያዩትን አይተው ለሕይወታቸው ሠግተው ዝም ብለዋል የሚል ነው?
አቶ አስፋው፦ በኔ ትሑት አስተያየት ከግለሰቡ ሰብእና ተነሥቶ፣ አንድ ሰው ምን ዐይነት ተግባር ለመፈጸም እንሚችል እና
እንደማይችል ለመመዘን ለማየት መነሣት ትክክለኛ የብየና መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ:: እኔን በሚመለከት ከነገርከኝ
የሁለተኛው ወገን መላምት እንዳጋጣሚ ሁኖ የተከሰተ ሐቅ አልነበረም:: ያመሸንበት አካባቢ ለዚህ ግብ የሚመረጥ ይሆናል
ብዬ አልገምተውም:: የሆነው ሁኖ፣ ያችን ምሽት በዓሉን የሚመለከት እኔ ያየሁትና ያስፈራኝ ክስተት አልነበረም:: ስለዚህ፣
አይቼ ዝም ያልኩት ወይም የደበቅሁት ነገር እንደሌለ በእርግጠኝነት እናገራለሁ:: ይኸን መቀበል አለመቀበል የእምነት ጉዳይ
ሊሆን ይችላል::
ነገር ግን፣ ከዚህ ዘልዬ አጋጥሞኝ የነበረ ቢሆን ኖሮ የሚለውን ማሰብ አያስልገኝም:: አላጋጠመም በቃ! ብዬ አቆማለሁ::
ፍቱን፦ ሰው በበዓሉ መሰወር እኔን ተጠያቂ አድርጓል የሚል ቅሬታ ወይ ምሬት አድሮቦታል;
አስፋው፦ ፈጽሞ! ኅሊናዬ ንጹህ እና የውስጥ ሰላም ያለኝ ሰው ነው :: ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ፣ በሕግ ፊት ከምኑም ነጻ የሆንኩ
ዜጋ ነኝ:: ከታወቁት ሁለት ወንጃዮቼ ሌላ የማውቀው ሌላ የለም:: የሚጠረጥር ቢኖር መብቱ ነው:: እውነቱን ፈላጊ ከሆነ
ይደርስበታል ብዬ አስባለሁ::
ፍቱን፦በዓሉን በተመለከተ ሕሊናዎ ነጻ ነው?
አቶ አስፋው፦ Absolutely, ምንም:: በበዓሉ ግርማ ጉዳይ ላይ ከሕሊና ዕዳ ነፃ ነኝ:: ለምኑ ብዬ እኮ ነው የምልህ? እንዲህ
አይነት ሁኔታ ውስጥ የሚጨምረኝን ነገር ለምን አደርጋለሁ? እኔ ሰዎች በጥረታቸው ሲሳካላቸው ደስ ይለኛል:: የሆነ
እርካታ ይሰማኛል፣ ይሄ ባህሪዬ ተቃራኒ ስሜትና ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎችን ያናድዳቸው ይሆን ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ::
እነሱ ተመኝተውት ያጡትን እኔ ሳልፈልግ አግኝቼ ይሆን?
ፍቱን፦ አቶ አበራ ለማ ጋር ከዚህ በፊት ቅራኔ ነበራችሁ?
አቶ አስፋው፦ እኔ ከእሱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቻለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም:: የተገናኘነው ኢትዮጵያ መጽሐፍ ድርጅት ሆኜ
“ሕይወትና ሞት” የምትለው መጽሐፍ እንዲታተምለት የበኩሌን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ:: የ“ማለዳ ስንቅ” የምትለዋን
ኩራዝ እንድትታተም አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ:: በድርሰት በኩል ግንኙነታችን ይሄ ነው::
አንድ ጊዜ ኩራዝ የጀመርናት መጽሔት የመጀመሪያው ሕትም የመሆኑ ጽሑፎች ሰዎች እዲያመጡልን በአዘጋጁተ በስብሐት
ገ/እግዚአብሔር ጥሪ ተደርጐ ስለነበር ጽሑፋቸውን ካመጡልን ሰዎች መካከል አበራ ለማ አንዱ ነበር::
የሆነ ቀን ስብሐት ቢሮዬ ይመጣና “ይሄንን ነገር አንብበው፣second opinion እፈልጋለሁ” ብሎ የአበራ ለማን ጽሑፍ
ይሰጠኛል:: አነበዋለሁ:: የተጻፈው “ሂስ” ተብሎ ነው:: ሂሱም የሚካሄደው በታዋቂው ገጣሚ በሰይፉ መታፈሪያ “የተስፋ
እግር ብረት” ውስጥ ባለ አንድ ግጥም ላይ ነው:: እንደአጋጣሚ “የተስፋ እግር ብረትን” ሰይፉ መታፈሪያ ሸልሞኝ እጄ ላይ
ስለነበር አውቀዋለሁ:: ሂሱን ሳነበው ትንታው ጥሩ አልነበረም:: ያን ጊዜ አበራ ለማ ገና የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ
መግባቱ ነበር መሰለኝ:: የተማረውን ተግባራዊ ለማድረግ ነው መሰለኝ ያንን ጽፏል:: መደምደሚያውግን ፍጹም ትክክል
ስላልነበረ ይሄንኑ ለስብሐት ነበርኩት:: ስብሐትም የእኔም ሃሣብ ነው ብሎ ተስማማ:: በሁለቱም መጽሐፎቹ ሳቢያ
እንተዋወቃለን በሚል ደውለን አናናግረው ብለን ደውዬ ነበርኩት:: በፍፁም አልተስማማም:: “ተሳስተሃል” አለኝ::
ፍቱን፦ አቶ አበራ ለማ በግጥሙ ላይ የሰጡት ድምዳሜ ምን ነበር?
አቶ አስፋው፦ የግጥሙ መልዕክት ብር ቁፈራ ነው የሚል ነበር የእሱ ድምዳሜ:: በእርግጥ ግጥም ገጣሚ ስለብር መቆፈር
ሊጽፍ ይችላል:: አበራን ወደዚያ ድምዳሜ የመራው ግን የሰይፉ አንዳንድ ፊደሎችን የመደጋገም ስልቱ ነው:: በዚያ ላይ
ተመስርቶ የፈጸመው ስህተት ነው እኔ የመሰለኝ::
(ግጥሙን ቀጥሎ ያለው ነው)
አድካሚ የሕይወትን መልክ ፍለጋ
እፍ እፍ፤ እፍ የጉሽ ገፈት
የጥራት ከለላ
እንትፍትፋት::
..
እፍ እፍ ስልባቦት
የወተት ላይ ውፍረት
እኝካት::
..
እፍ እፍ ግግርት
የውሃ ላይ ቅርፊት
አረንጉዋዴ በቀልት::
..
እንደ ጉሽ ገፈቱ
እንደ ስልባቦቱ
የውሃ ግግርቱ
..
እንደዚያ ደዚያ
እፍልኝ ምሥጢር ከለላ
ሰዋዊ ዐይነ – ጥላ::
..
የሕይወት ምሥጢር
በዘመናት ክምር
ቅበርብርብርብርብር
(እሱን ነው እምቆፍር)::
ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው (መስከረም 1969 ዓ.ም)
ፍቱን፦ ከዚህ ሁሉ በኋላ ልትግባቡ አልቻላችሁም?
አቶ አስፋው፦ ‹‹ተሳስተሃል››አለኝ:: ነገሩ እኔ እኮ የስነ ጽሑፍ ተማሪ ነኝ ነው:: “አይ በአንተ ድምዳሜ ያልተስማማሁት እኔ
ብቻ ሳልሆን የመጽሔቱ አዘጋጅ ስብሐትም ጭምር ነው፣ ስብሐትም እንደዚሁ ነው ያሰበው›› አልኩት:: “ሁለታችሁም
ተሳስታችኋል” ሲለኝ፣ “እኛ ስህተት ነው ብለን የምናስበውን መተው እንችላለን፣ ወይም ደግሞ ከComment ጋር
ልናቀርበው እንችላለን:: ‹‹እንዲህ ብለነው ነበር፣ አንባቢ ራስህ ፍረድ›› ብለን ማውጣት እንችላለን፣”ብዬው በመሐሉ፣‹‹
ገጣሚው ራሱ ስላለ ልደውልለት›› ስለው፣ ‹‹ደውልና ጠይቀው›› አለኝ::
ሰይፉ መታፈሪያን ደውዬ የአበራን ድምዳሜ አነበብኩለትና አስተያየቱን ጠየቅኩት::
“እንዴ ብሩን ከየት አመጣችሁት?” ነው ያለው:: ግጥሙ ውስጥ እኮ ብር የለም፣ ማለቱ ነው::
ይሄንን ነገርኩት::
አበራ ለማ አሁንም፣“እሱም ተሳስቷል” አለኝ:: ‹‹ባለግጥሙ?›› ስለው፣ ‹‹አዎን አያሲው እኮ ደራሲው ያላየውን የግጥሙን
አንድ መልክ ፈልፍሎ ያወጣል›› አለ:: ይሄንን መርህ እንደ መርህ አውቀዋለሁ:: እውነትም ይሆናል፣ ይሄኛው ግጥም ግን
በጣም ግልጽ ነው:: የመጀመሪያው አንጓ፣ የሁለተኛው፣ የሶስተኛው አንጓ በግልጽ ያስቀምጠዋል:: አራተኛው ላይ ሲመጣ
ያንኑ ነው:: ያ የሚቆፈረው የህይ ወትን ሚስጢርን ለማግኘት ነው፣ የሚል ነው:: ግጥሙ ራሱ ግልጽ ነው ››አልኩት:: ይሄ
ነው ያስቀየመው::
የነገሩ መቋጫ ይሄ ብቻ አይደለም:: ለካ ማታ ዩኒቨርሲቲ ሲሄድ ለጓደኞቹ “ሁለት ግጥም የማይገባቸው ሽማግ ሌዎች” እያለ
ወረፍ አድርጐናል:: ሌላው ክፋቱ በዚያን ሰዓት ፣ ስለ ሁለቱ “ግጥም የማይገባቸው ሽማግሌዎች” ማንነትና ስለየትኛው
ግጥም ማለቱ እንደሆነ እየጮኸ ሲያወራ በዚያ በኩል ያልፍ የነበረ አስተማሪው ይሰማዋል ፣አስተማሪው ደግሞ ግጥሙን
ያውቀዋል:: ወዲያውወደ አበራ ቀረብ ብሎ ፣ “የሚያሳፍሪው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ ? አንተ የእኛ ተማሪ ነህ መባሉ
ነው” ብሎት ይሄዳል:: ይኼ መቼም ቅስም የሚሰብር ነው:: ያቺ ትሆን እንዲህ የምታደርገው ብዬ አስባለሁ:: ያ ነው እንግዲህ
በእኔና በእሱ መካከል ተከሰተ የምለው ነገር::

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog