የብሔራዊ ፈተናዎች ኩረጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ በጥናት ተመለከተ

የአገሪቱ ብሔራዊ ፈተናዎች ላይ የሚታየው ኩረጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥናት ተጠቆመ፡፡ መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም.
‹‹በብሔራዊ ፈተናዎች ዙሪያ የሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ችግሮች፣ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርዕስ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የቀረበው የመነሻ ጥናት ችግሩ አሳሳቢ ነው ተብሏል፡፡ 

የአገሪቱን የነገ ዕጣ የሚወስኑና ችግር ፈቺ ይሆናሉ የሚባሉ ተማሪዎች በተደራጀ ሁኔታ ኩረጃ ላይ መትጋታቸው ከሥነ ምግባር ችግርነት አልፎ በሙስና የሚፈረጅበት ደረጃ ላይ መድረሱን፣ በኮሚሽኑ የሥነ ምግባር ትምህርት ባለሙያ በመሆን ለአሥር ዓመታት ያገለገሉትና የጥናቱ አቅራቢ የሆኑት አቶ ከበደ ሲማ ገልጸዋል፡፡ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደ አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ ላሉ ተቋማት ብቻ የሚተው አለመሆኑንም አቶ ከበደ ጠቁመዋል፡፡ 

‹‹የችግር ፈቺነት አቅምን፣ ባህልንና አመለካከትን በትምህርት አዳብረው ይወጣሉ የሚባሉ ተማሪዎች ችግር ፈጣሪዎች መሆናቸው በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትምህርት እናመጣለን ተብለው የተቀመጡ ግቦችን ይቀለብሳል፤›› ብለዋል፡፡
በብሔራዊ ፈተናዎች ላይ እየተፈጸመ ያለ ኩረጃ ጊዜው ባመጣው ቴክኖሎጂ (ሞባይል) እየታገዘ ቢሆንም፣ ኩረጃዎች በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በፈተና ጣቢያ አስተባባሪዎች፣ በፈታኝ መምህራን፣ በመስተዳድር ኃላፊዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በተለይም ስማቸውን በመሸጥ ጥሩ ገቢ ለማግኘት በሚጥሩ የግል ትምህርት ቤቶችም ጭምር እየተቀነባበሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በፈተና ጣቢያዎች ፀጥታን ለማስከበር የሚሰማሩ የፖሊስ አባላትም በመምህራን የተሠሩ የጥያቄ ወረቀቶችን በማቀበልና በተለያዩ መንገዶች በብሔራዊ ፈተናዎች ላይ ኩረጃዎች እንዲካሄዱ ሚና እንደሚጫወቱ ተጠቁሟል፡፡
መምህራን የጥያቄ ወረቀቶችን አባዝቶ ለተማሪዎች መበተናቸው፣ የመምህራንና የተማሪዎች ፈተናዎችን በጋራ መሥራታቸው፣ ፖሊሶችና ታዛቢዎች የመልስ ወረቀቶችን ወደ ክፍል ውስጥ ማስገባታቸው፣ መምህራን ተማሪዎችን ለቀቅ በማድረግና በቸልተኝነት እንዲኮራረጁ መፍቀዳቸው፣ ተማሪዎች መምህራንን ማስፈራራትና ብሎም በማሳደም ፈተናዎችን ማስተጓጐላቸው በብሔራዊ ፈተናዎች ላይ የተስተዋሉ የሥነ ምግባር ችግሮች ተብለው ከተጠቀሱት ዋነኞቹ ናቸው፡፡  
በመድረኩ አወያይ የነበሩት የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረ እግዚአብሔር በተያዘው ዓመት ኤጀንሲው ለብሔራዊ ፈተና አስተዳደር 68 ሚሊዮን ብር፣ ለሕትመት ደግሞ 53 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ ገልጸው፣ ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ በሚወጣበት የፈተና ሒደት ላይ የሚታዩት ችግሮች አሳሳቢ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፣ በተለያዩ ክልሎች የመስተዳድር አባላት ኩረጃን ለማቀነባበር ወደ ፈተና ጣቢያዎች ተደራጅተው ይገባሉ፡፡ በአንድ ክልል የሚኖር ሌላ ክልል ውስጥ ለሚፈተን ተማሪ በስልክ ፈተና እስከ መሥራት የተደረሰበት አጋጣሚም አለ ብለው፣ የግል ተፈታኞችም ቁጥጥር ጥብቅ አይሆንም በማለት ራቅ ያሉ የፈተና ጣቢያዎችን እየመረጡ ነው ሲሉ የችግሩ አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡ 
የተጠቀሱት ችግሮች ሙሉ ለሙሉ መኖራቸውን፣ መምህራን በግል ትምህርት ቤቶችና በሌሎችም በተለያዩ መንገዶች ተደልልው ኩረጃ እንዲካሄድ ተባባሪ እንደሚሆኑ፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መምህራን ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጫንያለው ታፈሰ ወርቅ ተናግረዋል፡፡
መምህራንን ባስጨበጡት ዕውቀት ሳይሆን ነጥብ እየተቀመጠ ከዚህ ነጥብ በላይ ያመጡ ተማሪዎች እየተባለ በተማሪዎች ቁጥር ብዛት መገምገም፣ የግል ትምህርት ቤቶች ትርፍ ተኮር መሆናቸው፣ ይህን ያህል አሳለፍን በሚል በክልሎች መካከል ጤናማ ያልሆነ ፉክክር መኖሩ፣ ለተጠቀሱት በብሔራዊ ፈተናዎች ላይ ለሚፈጸሙ ችግሮች ምክንያት ብለው ካስቀመጧቸው የተወሰኑት ናቸው፡፡ 
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ጥላሁን ታረቀኝ ደግሞ፣ የተማሪዎች የኩረጃ ሥልት እየረቀቀ  የመምህራንን የመቆጣጠር ብቃት እንዴት እንደበለጠ አስረድተዋል፡፡ ማኅበራቸው በሠራው ጥናት ‹‹ኔትወርክ፣ ንቅሴ፣ ፈንድሻ›› የሚባሉት ተማሪዎች እንደ ሁኔታዎች አመቺነት የሚከተሏቸው የኩረጃ ሥልቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ 
ራቅ ባሉ አንዳንድ ቦታዎች ምንም እንኳ መምህራን ኩረጃን መከላከል ቢፈልጉም ለሕይወታቸው በመፍራት ዝምታን የሚመርጡበት ሁኔታ መኖሩን፣ ለትምህርት ቤት ክብርና የክልልን ስም ለማስጠራት በሚል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ለኩረጃ አደራጅተው እንደሚልኩም አስረድተዋል፡፡ ‹‹አንድ ጐበዝ ተማሪ እነዚህን ይዘህ የመውጣት ኃላፊነት አለብህ ተብሎ ኮራጅ ተማሪዎች ተቆጥረው ይመደቡለታል፡፡ ለፈታኝ መምህራንም መደለያ ይሰጣል፡፡ ተማሪው ነው አስተማሪው የሚጠበቀው? ግራ ያጋባል፤›› ብለዋል፡፡ 
በተጠቀሱት መንገዶች ሲያጠፉ የተገኙ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን የሚቀጡበት አሠራር ቢኖርም፣ ተፈጻሚ የሚሆነው ቅጣት ለሌሎችም አስተማሪ እንዲሆን እንደማይደረግ አቶ ጥላሁን አስረድተዋል፡፡
በጥናቱ እንደተመለከተው በፈተና ጣቢያዎችና በፈተና ጣቢያ አስተባባሪ መምህራን አመራረጥ ላይ ያሉ ችግሮች ኩረጃዎች በተመቻቸ መንገድ እንዲካሄዱ በር ከፍተዋል፡፡ የፈተና ጣቢያዎች ጠባብና የተጨናነቁ በመሆናቸውና ሥርዓት ያስከብራሉ የተባሉ አካላት ሥርዓት በመጣሳቸው የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ፡፡ 
ፈተናዎችን ለመኮራረጅ አዳጋች በሆነ መንገድ የተለያዩ ኮድ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ፣ ድንገተኛ የፈተና ጣቢያዎች ቅኝት፣ በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ በተለይም በፈናዎች ወቅት በዘመቻ ግንዛቤ ማስጨበጥ ከተጠቆሙ የመፍትሔ ሐሳቦች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡   
በተለየ ሁኔታ ብሔራዊ ፈተናዎች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ሳይሆን፣ ከታች ጀምሮ ኩረጃ እንደ አንድ አማራጭ እየተያዘ በመሆኑ በጥቅሉ የአገሪቱ የመማር ማስተማርን ሒደት መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አስተያየታቸውን የሰጡም ነበሩ፡፡       
Source: Reporter

No comments:

| Copyright © 2013 Lomiy Blog