‹‹ግብፅ ስምምነት የተደረሰበትን ጉዳይ ለመቀልበስ እየጣረች ነው›› መንግሥት
የታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ሦስተኛ ዙር ድርድራቸውን ለመቀጠል የተገናኙት የኢትዮጵያ፣ የግብፅና ሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሳይግባቡ ቀሩ፡፡ ሦስተኛው ዙር ድርድር ያለውጤት ቢበተንም ውይይቱን በሌላ ጊዜ ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡
የታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ሦስተኛ ዙር ድርድራቸውን ለመቀጠል የተገናኙት የኢትዮጵያ፣ የግብፅና ሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሳይግባቡ ቀሩ፡፡ ሦስተኛው ዙር ድርድር ያለውጤት ቢበተንም ውይይቱን በሌላ ጊዜ ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡
የሦስቱ አገሮች ሚኒስትሮች ከዚህ ቀደም ሁለት ዙር ድርድሮችን በማካሄድ በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ መሆኑን የሚከታተል ኮሚቴ ለማቋቋም መስማማታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ቀሩ በተባሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሦስተኛ ዙር ድርድር ለማካሄድ በያዙት ቀጠሮ መሠረት ባለፈው ቅዳሜ ካርቱም የተገናኙ ቢሆንም፣ በግብፅ በኩል የቀረበው ሐሳብ ቀደም ባሉት ድርድሮች እልባት ያገኙ ጉዳዮችን የሚቀለብስ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አለማገኘቱን በኢትዮጵያ የውኃ፣ የመስኖና የኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሦስት አገሮች ሚኒስትሮች ከዚህ ቀደም በነበሩ ሁለት ድርድሮች ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግና ተግባራዊነቱን የሚከታተል ኮሚቴ ለማቋቋም ስምምነት የደረሱበት ጉዳይ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ፈቅ፣ በሦስተኛው ዙር ድርድር ይህንን ኮሚቴ የሚቆጣጠር ሌላ ዓለም አቀፍ አማካሪ ይቋቋም የሚል ሐሳብ ግብፅ ይዛ በመቅረቧ ላለመግባባቱ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል እንዲቋቋም የተስማሙበት ኮሚቴ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ለመተግበርና ተግባራዊነቱን መከታተል መሠረታዊ ኃላፊነቱ ሲሆን፣ ሦስቱን አገሮች የሚወክሉ ዜጎች ብቻ የኮሚቴው አባላት እንደሚሆኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የኮሚቴው አባላት ስብጥርን በተመለከተ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ ልዩነት ተንፀባርቆ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን የኮሚቴው አባላት በሦስቱ አገሮች የሚወከሉ ዜጎች ብቻ ይሁኑ በሚለው የኢትዮጵያ አቋም ላይ ስምምነት ተደርሷል፡፡ ይህ ኮሚቴ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ የውጭ አማካሪ ቅጥር የመፈጸምና አማካሪው የሚያቀርበውን ሐሳብ ገምግሞ የውሳኔ ሐሳብ የማቅረብ ኃላፊነት እንደሚኖረው፣ ለዚህና ለሌሎች ኃላፊነቶቹ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ሦስቱ አገሮች ይሸፍኑ በማለት ተደራዳሪዎቹ ተስማምተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሦስተኛው ዙር ድርድር ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ይነሳሉ ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም፣ የግብፅ ተደራዳሪዎች ተጨማሪ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት እንዲቀጠር መጠየቃቸውን አቶ ፈቅ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ግብፆች እንዲቀጠር የጠየቁት ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ከዚህ ቀደም ስምምነት የተደረሰበት ኮሚቴ ኃላፊነቶችን በበላይነት የመከታተል ድብቅ አጀንዳ እንዳለው መረዳት የተቻለ መሆኑን አቶ ፈቅ ገልጸዋል፡፡
‹‹አማካሪ ለመቅጠር ቅጥሩን የሚያማክር አማካሪ ድርጅት መቅጠር ተቀባይነት የሌለው አሠራር ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊነት ለመከታተል የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች በቂ ናቸው፤›› የሚል አቋም በኢትዮጵያ በኩል መያዙን፣ በዚህ ላይ መግባባት ባለመቻሉም ድርድሩ መቋረጡን አስታውቀዋል፡፡
‹‹በግብፅ በኩል ድብቅ ዓላማ ካልተያዘ በቀር አማካሪ ለመቅጠር ሌላ አማካሪ መቅጠር ታይቶ አይታወቅም፤›› ያሉት አቶ ፈቅ፣ ጉዳዩ ግን ተደጋጋሚ ውይይትን የሚጠይቅ በመሆኑ ለቀጣይ ውይይት በመስማማት መበተኑን ገልጸዋል፡፡ ቀጣዩ ውይይት መቼ እንደሚካሄድ ቀን ባይቆረጥም በግብፅ በኩል ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ድርድሩ የሚካሄደው በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ቢሆንም የሱዳን መንግሥት የህዳሴውን ግድብ ጠቀሜታ በመገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋምን ማራመድ መርጧል፡፡ ይህ በመሆኑም ድርድሩ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው በዋናነት በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል መሆኑን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ካቀረቡት ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡
Source: Reporter
No comments: